የልጥፍ ይዘት
መገናኛን እንደ ጦር እፈራው ነበር! (birthday eve confession) ያ ጊዜ አልፎ አሁን የማልፍ የማገድምበት ቦታ መሆኑን ሳስብ ፈገግ እላለሁ።...ነገሩ እንዲህ ነው። ከሦስት አመት በፊት ገና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እንደገባሁ ፤ ወቅቱ ለእኔ አስደሳችም ከባድም ነበር። ስመኘው እና ስተጋለት ወደነበረው ዩኒቨርስቲ ገብቼ መማር መቻሌ፣ በማህበራዊ ትስስር ገጽ (ፌስቡክ) የተዋወኳቸውን ወዳጆቼን በአካል እያገኘሁ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ መቻሌ እና ስቋምጥላቸው በነበሩ የጥበብ ድግሶች በተለይ በዋልያ መጽሐፍ በየሳምንቱ ይዘጋጅ የነበረው ከደራሲያን ጋር የመተዋወቅ እና መጽሐፍ የማስፈረም ዝግጅት ላይ መታደም መቻሌ ወቅቱን አስደሳች ያደረጉልኝ ጉዳዮች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ለከተማው አዲስ መሆኔ ፣ የታክሲ ሰልፍ እና ትርምስ ፣ የአየር ሁኔታው ከነበርኩበት ቆላማ ከባቢ አንፃር ከባድ ብርድ ያዘለ መሆኑ ፣ በኮቪድ 19 የተዘጉ በሮች እንደተከፈቱ የገባን ባቾች በመሆናችን የባከነ ጊዜን ለማካካስ የነበረው የትምህርት መደራረብ እና ጥድፍያ 'የፍሬሽ ማን' ህይወቴን ከባድ አድርገወታል። በዛ ላይ 'ሲንየር' ተማሪዎች ቀለል ያለ የሚሉት ለእኔ ግን አሁን ሳስበው እስኪያስቀኝ ድረስ ያስደነበረኝ ግጭትና ግርግር ግቢ ውስጥ ተፈጥሮ ስለነበር የሚሰማኝ ስሜት ድብልቅልቅ ያለ ነበር። ላለው ይጨመርለታል የሚባለው ነገር ለእኔ የሰራው በመጥፎ እስኪመስለኝ ድረስ ያለብኝ ድብልቅ ያለ ስሜት ሳያንስ ከጓደኞቼ ጋር ደባሪ በሆነ መልኩ ስልኮቻችንን እና በእጃችን የያዝነውን ገንዘብ ተዘረፍን። ጩቤ ምናምን ነበረው ዝርፍያው። ሌቦች ዘርፈውን ሲያመልጡ ፖሊሶች ደረሱ። መሳርያቸውን አቀባብለው እጃችንን ወደላይ አንስተን ጀርባ ለጀርባ ተደጋግፈን እንድንቆም ካደረጉ በኋላ የተዘራፊ ሳይሆን የዘራፊ 'ትሪትመንት' ሰጡን! ሃዬ👍 ለተወሰኑ ደቂቃዎች እየወተወትን ተዘራፊ መሆናችንን ማስረዳት ነበረብን። መታወቂያ ባንይዝ ኖሮ ዱላ ሳንቀምስ የምንቀር አይመስለኝም። ወደ ፖሊስ ጣብያ ስናመራ በሚገርም ሁኔታ "ከተዘጋው ዶሴ" ላይ መቅረብ የነበረባቸው የዝርፍያ ታሪኮች ከራሳቸው ከፖሊሶቹ እየተተረከ ቀላል ነገር እንዳጋጠመን እና እንድናመሰግን ተነገረን። ይባስ ብሎ አንዱ ፖሊስ ማጅራቱ ላይ እጁን እንደ ዱላ እያሳረፈ እንዴት ሃንግ እንደተሰራ አጫወተን። ሃዬ👍 ብቻ ተዘርፈን ፣ ብዙ ተንገላተን ያቀን አለፈ።(ፖሊሶቹ እንዳሉን በሰላም አለፈ) ከዛ በኋላ ከግቢ መውጣት እየደበረኝ መጣ። በፊት የምስቅባቸው የዝርፍያ 'ሜሞች'ን በቀልድ መልክ ማየት አቆምኩ። አስገዳጅ የሆኑ ከግቢ የሚያስወጡ ጉዳዮች ሲኖሩ ደግሞ አጠገቤ የቆመን ሰው ሁሉ እንደሌባ የማይ ጠርጣራ ሆንኩ። ጥርጣሬው ከጥንቃቄ ከፍ ያለ ነበር። አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እጅግ ተራ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ያስፈሩኝ ፣ ያስጨንቀኝ ነበር። ስሜቱ ቀላል አልነበረም። የልብ ትርታዬ እስኪዛባ፣ እስኪያልበኝ እና አተነፋፈሴም ልክ እስካይሆን ድረስ ነበር። ከሰፈሮች ሁሉ መገናኛን በተለየ ጠላሁት። እንደጦር እፈራው ጀመር። ቀጠሮዬ መገናኛን ከነካ መሰረዝ ልማዴ ሆነ። በዚህ ስሜት ውስጥ እያለሁ የመጀመርያ መንፈቅ አመት ተጠናቀቀ እና የትምህርት መስኬን ለይቼ ወደ ውቢቷ ቢሾፍቱ(ደብረዘይት) ተዘዋወርኩ። አንዳንድ ስሜቶች ልክ እንደ ረመጥ ናቸው። የጠፉ የመሠሉ ነበልባሎች! አመዳቸውን እፍ የሚል ሲገኝ የሚነዱ፤ የሚንቦገቦጉ! የሐይቅ ከተማዋ ቢሾፍቱ እርጋታ ፣ ነፍስን የሚዳስስ ነፋስ እና ያለሁበት ኮሌጅ መጠነኛ ተማሪ ያነው ስክን መሆን ሁሉን ነገር አስረስቶኝ ነበር። ለመገናኛ ያለኝን ጥላቻ እና ፍራቻን እፍ ብሎ ድጋሚ ያቀጣጠለው ወደዛ የሚወስደኝ ተደጋጋሚ ቀጠሮ ሲመጣ ነው። ችግሬን የሚያውቅ የለም። እስቲ አስቡት?! ምንስ ብዬ መገናኛ መሄድ እፈራለሁ! እዛ ያለ ሰው ሁሉ ሌባ ይመስለኛል! እላለሁ? እንዳልምል አብሮኝ የተዘረፈው የልብ ወዳጄ በመጠኑ ይህን ስሜቴን ያውቃል! በዚህ ልክ የገዘፈ መሆኑን መረዳቱን ግን እጠራጠራለሁ። ብቻ ቀጠሮዎቼን ከግቢ ጓደኞቼ አንዱ ወደ መገናኛ የሚያስኬደው ጉዳይ ሲኖር ከእሱ ጋር ትይዩ እያደረኩ አብሬው እሄዳለሁ። ግራ ቀኜን እየተገላመጥኩ፣ እያንዳንዱ ከሰዎች ጋር ያለኝን ንክኪ እየቆጠርኩ የልብ ምቴ ተዛብቶ ደርሼ እመለሳለሁ። ብቻዬን መሄድ ይደብረኛል እያልኩ ያለ እቅዳቸው ይዣቸው መገናኛ የተገኙ ወዳጆቼም ነበሩ። እንዲህ እንዲህ እያለ ሰው ማስቸገር ፣ ግፋ ሲልም መለማመጥ እየሰለቸኝ መጣ። ቆም ብዬ ሳስብ ይህ ፍርሃት ችላ ካልኩት ሊወሳሰብ እንደሚችል ገባኝ። በነገራችን ላይ ይህንን ገጠመኜን እንድጽፍ የገፉኝ "የአማኑኤል ሆስፒታል ተረኮች" የተሰኘው የዶ/ር ዮናስ ላቀው መጽሐፍን ሳነብ ያየኋቸው እንደ ቀልድ ጀምረው ችላ በመባላቸው ወደ ውስብስብ ህመም የተቀየሩ የፍርሃት ታሪኮች ናቸው። ስለ አእምሮ ጤና በተለያዩ አጋጣሚዎች አንብቤ ባውቅም በእውነተኛ ታሪክ የተዋዛው ይህ መጽሐፍ ብዙ እንዳስብ አድርጎኛል።(እንድታነቡት ግብዣዬ ነው) ወደ መገናኛ እንመለስ?! ይህን መጠን አልባ ፍርሃቴን ለማሸነፍ የወሰንኩት እሾህን በእሾህ በሚለው መርህ ነው። ብቻዬን በድፍረት ወደ መገናኛ በመሄድ! ዝም ብሎ እግሬ እስኪዝል በፍርሃት ቀጠናዬ በመዞር!! ያ ቦታ የፍርሃቴን ያክል ከባድ እንዳልሆነ ልቤ ያውቀዋል ፤ ቀልቤ እንዲያምነው ግን ማሳየት ነበረብኝ። መሐመድ እንድሪስ ካሳ አንድ የምወዳት ግጥም አለችው: እርግጥ ነው ቁስልህ በርክቷል እንዳሸዋ ዘር ግን አይበጅህም ደዌ መዘርዘር። ሂድ ወደ ቁስልህ ዝለቅ ቀውስጡ እዛ ነውኮ እነ ብርሃን እነበረከት የተቀመጡ። እኔም ከፍርሃቴ ለመዝለቅ ወሰንኩ። የወሰንኩ ቀን ምሽት እንቅልፍ አልወሰደኝም። ጠዋት ወደ መነሃሪያ ስሄድ እያላበኝ ነበር። ለማንኛውም ብዬ በኪሴ በዛ ያለ ብር ይዣለሁ(ትንሽ ከተደናበርኩ ራይድ ለመጥራት እኮ ነው።😂) ስልኬን በ bottom ስልክ ቀይርያለሁ። (ቢጠፋም ይሄ ይጥፋ ነው ነገሩ) የጓደኞቼን ስልክ እንደ ድሮ ዘመን በወረቀት ጽፌ ይዣለሁ። ምንም የማደርገው ሳይኖረኝ መገናኛ ደረስኩ። በቃ አዙሪት እንደያዘው ሰው ዞርኳት። ይኸው ይሄ ነው መገናኛ እላለሁ ለራሴ። ቀስ በቀስ ፍርሃቴ ሲለቀኝ ታወቀኝ። የልብ ምቴ እስኪስተካከል ፣ መድከም እና መራቤ እስኪታወቀኝ ዞርኩ። እልህም፣ ደስታም ውስጤን ተሰማኝ። የሆነ አይነት እርካታ ነበረው። ድክም ሲለኝ ለጓደኛዬ ደውዬ የአራት ኪሎ ታክሲ የቱ ጋር እንደሚያዝ ባውቅም ሰው ደጋግሜ እየጠየኩ በራሴ ላይ ድል በመቀናጀት መንፈስ የፍርሃት ቀጠናዬን ተሰናበትኩ። የፍርሃት ረመጤ ላይ ወሃ ቸለስኩበት። መገናኛ እንደማንኛውም ሰፈር ሆነኝ። ይህ በህይወቴ የማልረሳው ታሪኬ ሆኖ ተጻፈ። መጠኑ እና ሁኔታው ቢለያይም በእንደ እኔ አይነት አጋጣሚ ያለፈ ወይንም እያለፈ ያለ ሰው ይኖራል። ሌሎች በቀላሉ የሚያደርጉት ነገርን ለማድረግ ከልኩ ያለፈ ፍርሃት ካላችሁ ቆም ብላችሁ ማየት ያለባችሁ ይመስለኛል። እኔ የስነ ልቦና ባለሞያ አይደለሁም። ነገር ግን ያልጠበቅናቸው ገጠመኞች ሳይታወቀን 'ትሮማታይዝ' እንደሚያደርጉን ከገጠመኜ ተምርያለሁ። እንዲህ እንዲህ አድርጉ የማለት ድፍረቱ ባይኖረኝም። ሲያጋጥም ግን ለቅርብ ወዳጅ ማማከር እና መፍትሄ መፈለግ እንደ ረመጥ አለባብሶ እና አፍኖ ከማስቀመጥ ይሻላል ባይ ነኝ።