የልጥፍ ይዘት
Hi! እንዴት ዋልክ? እንዴት ዋልሽ? አለሁ! ዛሬ ጥሩ የማንበብ mood ላይ ነኝ ብታይ! ምን እያደረክ ነው? እያነበብኩ! I see የማንበብ mood ላይ ከሆን አንድ ሐሳብ ላጋራሽ?! በደስታ😊 ናፖልዮንን ታውቂው ይሆን! በአውሮጳ ስሙ የገነነ ንጉሰ ነገስት ነበር። በታሪክ ጸሃፊያን የሚጎመዥ እና የሚጻፍ እልፍ ታሪክ ባለቤት ነው። በነገሰበት ዘመን የነበሩ ነገስታት ሁሉ በፍርሃት የሚሽቆጠቆጡለት ነበር ናፖልዮን ቦናፓርት። አንድ ግዜ አገልጋዩ ከእልፍኝ ስነስረዓት በፊት ቀደም ብሎ እንዲደርስ ይነግረዋል። ነገር ግን አገልጋዩ እጅግ ያርፍድና ናፖልዮን በንዴት ደሙ ይፈላል አገልጋዩ በደረሰ ጊዜም ለምን እንዳረፈደ በቁጣ ይጠይቀዋል። ይሄኔ አገልጋዩ "ነገስታቱ በር ላይ እየተጋፉ አላሳልፍ ብለውኝ" ብሎ ንዴቱን በፈገግታ አበረደው ይባላል። ናፖልዮን ነገስታት ከእልፍኙ ሊገቡ የሚጋፉበት ንጉሰ ነገስት ነበር። በእርሱ ዙርያ የተጻፉ መጻህፍት 200 ሺ ይደርሳሉ ይባላል። ስለ ታሪኩ ሲነሳ ሁለት አይነት ሰዎች ይስታዋላሉ። ፊታቸው የሚፈካ እና ፊታቸው የሚጠቁር። ናፖልዮን በነገሰበት ዘመን ህልሙ አንድ ነበር..."በአንድ ንጉሰ ነገስት ውስጥ ሆና ካልተዳደረች በቀር አውሮፓ ሰላም አታገኝም"ና በተለያየ ባህል እና ነገስታት የምትመራውን አውሮፓ አንድ አድርጎ ጦርነትን ማስቀረት። በዚህ አላማ ምክንያት ታሪኩ ሲነሳ ፊታቸው የሚፈካ ብዙ ነው። ጦርነትን ለማስቆም ብሎ ያደረጋቸው ጦርነቶች አውሮፓን ደም አቃብተዋል። እስካሁን ፈረንሳይን የጎሪጥ የሚያዩ ሀገሮች እና በጭካኔ የሚያነሷት እንዲኖሩ ምክንያት ሆናል። ናፖልዮን የጦርት አምካኝ ሳይሆን የጦር ሱሰኝነት ምሳሌ ነው ብለውም ታሪኩን የሚያጠለሹ። ፊታቸውን የሚያጠቁሩ ጥቂት አይደሉም። የሆነው ሆነ እና ልነግርሽ የፈለኩት ዋናው ነገር ታሪኩን ሳነብ ቴዎድሮስ ትዝ አለኝ። ባለ ጉንጉኑ ፣ የቋራው አንበሳ ፣ መቅደላ አፋፍ ላይ ያበራው የኢትዮጵያ ኮከብ ፣ ወንድ አንድ ሰው የተባለው ፣ መይሳው ካሳ። ናፖልዮን እና አጼ ታዎድሮስ በዋናነት ሁለት የሚያገናኛቸው ነገር ነበር። የመጀመርያው ሁለቱም ከደሃ ቤተሰብ የተገኙ ናቸው። ናፖልዮን የተማረው በመንግስት እየተደጎመ ነው። ጓደኞቹ ከዘመዶቻቸው ዘንድ ገንዘብ ሲላክላቸው እሱ ግን ዘመዶቹ ሊረዱት ባለመቻላቸውና ከጓደኞቹ በማነሱ በሐዘን በብስጭት ይኖር ነበር። አጼ ቴዎድሮስም የኮሶ ሻጭ ልጅ ነበር። ማንም ለንግስና ያሰበው አልነበረም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ በሽፍትነቱ ዘመን ከእቴጌ ምንትዋብ ዘንድ የነበር ወንድይራድ የሚባል አዝማች(ማዕረጉን እርግጠኛ አይደለሁም።) ያን የኮሶ ሻጭ ልጅ አንጠልጥዬ ባላመጣው ብሎ ንግስቱ ፊት ፎክሮ ሄዶ ዘምቶበት ነበር። ነገር ግን መይሳው ካሳ ጎበዝ ጦረኛ ነበር እና አሸነፈው እና መራራውን የኮሶ ፍሬ በእንብርክክ ፈጭቶ እንዲጠጣ በማድረግ የተዘባበተበትን ወንድይራድ ለሱሙ በማይመጥን ክብረ ነክ በሆነ መልክ እንዲሞት አደረገው። ሁለቱም የደሃ ልጆች። ቁጣቸው የጋለ፣ ሽንፈትን የማይወዱ እና ቆራጥ ቆፍጣና ጦረኞች ነበሩ። በድል ላይ ድል እያደረጉ በዙርያቸው ያሉ ጉልበተኞችን እንቅልፍ እንዲያጡ አድርገዋል። በነገሱ ጊዜም ከፍርሃታቸው የተነሳ የሚንቀጠቀጡላቸው ብዙ የጦር መሪዎች ነበሯቸው። ሁለተኛው የሚያመሳስላቸው የአወዳደቃቸው ነገር ነው። ከበደ ሚካኤል ታላላቅ ሰዎች በሚለው መጽሐፉ የናፖልዮን ውድቀት ሲያነሳ "....ነገር ግን ናፖሌዎን ይህን ከመሠለ ከፍ ካለ ክብር ለይ ተቀምጦ በማየታቸው በዘመኑና በዙሪያው የነበሩት ሰዎች በልባቸው ጥልቅ የሆነ ቅናት ተፈጥሮ ነበር፤ የሚታዘዙትም በፍርሃት ነበር። ነገር ግን ናፖሌዎን የሚፈራ ሰው መሆኑ ቀርቶ ስለ ታማኝነትና ስለ ውለተኝነት ብቻ ሊያገለግሉት የሚገባቸው የሆነበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ ፍቅራቸው ወደ ጠላትነት ተለወጠ።" ሲል ይገልጸዋል። ናፖልዮን በነገሰበት ዘመን ሁሉ ከሀይሉ የተነሳ እና ካለመሸነፉ እንጂ አላማውን ደግፈው የታመኑለት ጥቂት ነበሩ። የውድቀጡ ጉድጓድ በተጫረ ጊዜ ምሰው የሚያሰፉት ገፍትረው ሊጥሉት እና ሊቀብሩት በቦታውም ለመንገስ የሚመኙ የራሱ ወገኖች ነበሩ። ወንድሞቹ ሳይቀር ካስከመጣቸው ከፍታ ላይ ሆነው የሱን ማማ ተመኝተዋል። ሊያወርዱት እና በቦታው ከፍ ሊሉ ቋምጠዋል። እርግጥ የነበረው ግርማ ሞገስ ክብር እና ዝና ለኔም የሚያስብልና የሚያስመኝ ነበር። ነገር ግን እርሱ የደረሰበትን ማማ ለመመኘት ያስቻላቸው ከፍታ ላይ ያወጣቸው እርሱ ራሱ ናፖልዮን ቦናፓርት መሆኑን ዘንግተው ኑሮ ሊጥሉት ሲታገሉ ይዘውት ወድቀዋል። አጼ ቴድሮስ ለሀገሩ ቀናኢ ነበር። ኢትዮጰያ በስልጣኔ ከፍ ብላ ከሩቅ እንደሚሰማቸው የነናፖልዮን ሀገራት ሁሉ ስሟ እና ክብሯ ገናና እንዲሆን ይመኝ ነበር። ለዚህም ሳይታክት ሌተ ቀን ይለፋል። ሆኖም ግን ዝናና ክብር አብረውት ባሉ ባለ ሟሎች ዘንድ የተፈራ እንጂ የተወደደ አልነበረም። አጼ ቴዎድሮስ ከፍ ባለ ቁጥር ክፍታውን ሊቀሙ የሚሹ ብዙ ነበሩ። ከእንግሊዝ ጋር በነበረው ጦርነት። የመይሳውን የሞት መንገድ ለእንግሊዞች ጠርገው እያደላደሉ የመጡት የራሱ ወገኖች ናቸው። በላይ ሲሄድ በታች ጦርነት እያነሱ ሀይሉን ያደክሙት ነበር። መቅደላ እስኪደርስ ድረስ። ሽንፈት የማይወደው እና ከጠላቶቹ ጭብት ውስጥ ትንፋሹን በጁ ነጥቆ በገዛ ጥይቱ እስኪሞት ድረስ! ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ስሌ ስንብቱ "የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ" በተሰኘው ግጥሙ ስያነሳ አጼ ቴዎድሮስ እንዴት መከዳት እንዳጎሳቆለው እንዲህ አስፍሮታል። "መች ትተርፊያለሽ አትዮጵያ፣ ህዋስሽ አብሮኝ ካልሰራ አንገትሽ ብቻ መቅደላ አፋፍ ወጥታ ብታበራ የቀረ ሰራ አካላትሽ በየጢሻው ተዘርሮ ከአባት በወረስሽው ንፍገት ነብዞ ደንዝዞ ተቀብሮ በአጉል ወጌሻ ታጅሎ እጅና እግርሽ ታሽቶ ዝሎ እኔን ለጥንባንሳ ጥሎ ከደቀቀ ከደከመ ክንድሽ አልነሳ ካለ ሞት እንጂ ለኔስ ምን አለ?" ይህም ሀገሩ አብራው ብትሆን ሩቅ ከሆነ ህልሞ ይደርስ ይችል እንደነበር ነገር ግን ህዋሷ አብሮ ባለመሥራቱ ተግባር የሌለው ሀሳብ ብቻ ሆኖ እንደቀረበት ያመልካች ነው። በአጠቃላይ ናፖልዮን እና አጼ ቴዎድሮስ እንግዲህ ጥቂት ብልጭ ብለው ከሚጠፉ ነገር ግን እድሜ ልካቸውን እያየናቸው ከምንቆያቸው ሲብለጨለጩ ከምናያቸው ከዋክብት በላይ ደጋግመን የምናነሳቸው አብሪ ኮኮቦችን ይመስላሉ። የበሩት ጥቂት ጊዜ ቢሆንም ተንቀሳቅሰዋልና በፈጠሩት ለውጥ አለም ብልጭታቸውን ሲያነሳው ይኖራል! ጀግና አይሞትም አይደል የምንለው? "የሚከርም ነው። ያያዘሰክበት መንገድ 🤝" እንዲሁ 😊 የቴዎድሮስ ታሪክ ላይ ግን አንድ ተጨማሪ ነገር ማንሳት ፈልጋለሁ። ሁለቱን አያይዤ ከናፖልዮን ጋር እንዳነጻጽራቸው ያደረገኝ ዋና ምክንያት እሱ ስለሆነ። በሃይል ወይንም በጉልበታችን አልያም ልክ በማይገኝለት እውቀታችን የምንመራው ሀገር ከባድ እንደሆነ። ማለት ሰዎች በተፈጥሯቸው ሊያሸንፉን እንደሚፈልጉ ማመን አለብን። ስልጣኑ የመነጨው ከእነርሱ ጭምር እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ አለብን። ሀገሪቱ እየቀጠለች ያለችው እነርሱም ባዋጡት ጡብ እንጂ እኛ ባለን ፍላጎት ብቻ እንደሆነ እንዲሰማቸው ማድረግ የለብንም። ስልጣን ህዝብ የኔ ካላለው ከንቱ ነው። ማለት ሀሳብ ትክክል ቢሆንም ባይሆንም ህዝቡ የኔ ነው ካለ ሀሳቡና ስልጣን ይቀጥላል።