የልጥፍ ይዘት
ከአራት አመት በፊት የተጻፈ በፌስቡክ ትውስታ ድጋሚ ለማጋራት ወደድኩ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ሂሳብ፣ አከባቢ ሳይንስ ፣ ጋሞቶ ዶና እና ስፖርት እንዲሁም ስዕል ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ያስተማሩኝ ቲቸር ዩፋይሳ የሚባሉ መምህር ናቸው። በሳምንት ከሶስት ወይም አራት ክፍለ ግዜዎች ውጪ አብዛኛውን ግዜያችንን ያሳለፍነው ከእርሳቸው ጋር ነው። አንዱ ክፍለ ግዜ አልቆ ሲደወል በሉ አሁን ሂሳብ ደብተራችሁን አውጡ ብለው ሌላኛው ክፍለ ግዜያቸውን ይቀጥላሉ። ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የርሳቸው ሀላፊነት የነበርነው የ C ክፍል ተማሪዎች ነበርን A እና B እንዲሁም D ክፍል የየራሳቸው መምህራን ነበራቸው። በዚህም ምክንያት ይመስለኛል ቲቸር ኡፋይሳ ሁላችንንም የክፍላቸው ተማሪዎች ጥንቅቅ አድርገው ያውቁናል። ለምሳሌ ክፍል ውስጥ ጸብ ከተነሳና ጥፋተኛው ማን እንደሆነ ማጣራት ከፈለጉ የሚጠይቁት አበሰብ የሚባል የክፍላችን ጨዋ እና ሁሉን ነገር በአንክሮ የሚከታተል ልጅ ነው። አበሰብ ተጠርቶ የመሰከረው ነገር ላይ የሚከራከር አልነበረም። በሌላ በኩል ደግሞ ጥቁር ሰሌዳችን ላይ ማስታወሻ ጽፈው እንድንገለብጥ ካዘዙን በኋላ ማስረዳት ለመጀመር መጨረሴን የሚያዩት እኔን ነው(በወቅቱ የክፍሉ ቀርፋፋ ጸሐፊ እኔ ነቀርኩ) እንዲሁም ማን በየትኛው ክፍለ ግዜ ቶሎ እንደሚገባው ማን ቀስ እንደሚል በሚገባ ያውቃሉ። የሚያጎርሱንም በምንችለው ልክ ነበር። ዛሬ ያነሳኋቸው የ Yordanos Almaz Seifu "መንገደኛ አንድ" መጽሃፉ ላይ ስለ ትምህርት አሰጣጣችን ድክመት ከጀርመኑ የመዋለ ህጻናት ጉብኝቱ ጋር እያነጻጸረ ባወሳበት ገጹ "በሌላ በኩል ደግሞ መምህሮቻችን ይሠሩበት ከነበረው ሁኔታ እና ከሚያገኙት ክፍያ አንጻር እኛ ከእነርሱ የተሻልን ዜጎች እንድንሆን ሲጥሩ እንዲኖሩ እና ያለበቂ እርካታ እያለፉ እንደሆነ ይሰማኛል። በተለይም የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ መምህሮቻችን ከዕውቀት በላይ እውነት፣ከቁጥር በላይ ሥነምግባርን እና የሀገር ፍቅር አሻራቸውን ተማሪዎቻቸው ላይ ለማተም ሲተጉ እና በሕይወት እያሉ ፣ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ እንዳለው ' የእጃቸውን ዘገር' ለመበተን ሲጥሩ እንደነበር አስታውሳለሁ።"(መንገደኛ አንድ-ገጽ 52/*17/) ላለው ዮርዲ እኔም መምህር ኡፋይሳን አስታውሳለሁ ለማለት ነው። አብረውን በሚቆዩት ረጅም ከፍለግዜያቸው ከአካዳሚክ ትምህርት ይልቅ ስነምግባርን መግበውናል። እንደማስረጃ በክፍላችን ውስጥ አንድ ተማሪ በተደጋጋሚ ከክፍል ከቀረና የሰፈሩ ልጆች እንደተመመ ከነገሩን ከመምህር ኡፋይሳ ጋር በሰልፍ ሆነን እቤቱ ድረስ በመሄድ እንጠይቀው ጸሎት እናደርግለትም ነበር(ልጆች እኛቤት መጥተው እንዲያ እንዲያደርጉ በታመምኩ ብዬ ተመኝቼ አውቃለሁ። ክፍል ውስጥ ያለ ሁሉም ተማሪ ሁለት እስክሪብቶ ይዞ ትምህርት ቤት እንዲመጣ እና እስክሪብቶ የገነፈለበት ተማሪ ባገኘ ግዜ እንዲሰጠው ይነግሩን ነበር። ስለዚህም አንድ ተማሪ ትርፍ እስክሪብቶ ያለው ሲል እኔ እኔ እያልን እንሽቀዳደማለን። ከሁሉም የማልረሳው፤ በአንድ ወቅት መምህራችን ለተከታታይ ሁለት ቀናት ከትምህርት ቤታችን ቀሩ።ያው ሁሉን በሚባል ደረጃ እርሳቸው ስለሚያስተምሩን ትምህርት ሳንማር ዋልን። በሶስተኛው ቀን ግን ከሰፈራቸው ልጅ መታመማቸውን ሰማን። ልክ የወደቤት ሰዓት ሲደርስ ተሰልፈን ቤታቸው ሄድን ተማሪ ሲታመም እንደምናደርገው ጸለይንላቸው። ቲቸር ዩፋይሳ ያኔ ባልገባኝ ምክንያት አለቀሱ(አሁን ሲገባኝ የዘሩት በቅሎ ቢያዩ ነው) የተማሪዎቻችሁ ነገር የሚገዳችሁ መምህራን ሁሉ ምስጋናዬን እነሆኝ።🙏 አሻም! @Hasab_2016