የልጥፍ ይዘት
ስለ ነጭ ወርቅ ላወራችሁ ነው! ወርቅ የሀብት፣ የጥሪት መገለጫ ነው። እኔ የማወራችሁ ነገር ነጭ ወርቅ ያሰኘው ግብሩ ነው። በበረሃ መኖርን የሚቻል ያደረገ በኢትዮጵያ ከቆላማው ሀረርጌ ጀምሮ እስከ አለማችን ዝቅተኛው ስፍራ የአፋር ስምጥ ሸለቆ ድረስ ተወዳጅ የሆነ፣በጠንካሮቹ፣ ጥርሰ ነጫጮቹ፣ ሀገር ወዳዶቹ ባለ ሽርጦች፣ የዘመናት ባህል ባለቤቶች እና የሰው ዘር መገኛን ስፍራን ሐሩር ክብደት ለአኗኗራቸው አሰግደው በሚኖሩት የአፋር ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ፣ ቦረናና ከረዩ ህዝቦች በፍቅር የሚጠጣ። የበረሃው መርከብ ከተባለው የጽናት ምሳሌ፣ ከግመል የሚገኝ! አዎን የማወራው ስለ ግመል ወተት ነው። ስለ በረሃው ነጭ ወርቅ! የግመል ወተት ነጣ ያለ በሠጠኑ ክሬም የሚመስል ቀለም ያለው ወተት ነው። ቀለሙ ከላም ወተት ጋር ብዙም የሚራራቅ አይደለም። ጣዕሙ ወተቱን የምትሰጠው ግመል ለመብላት እንደምታዘወትረው እፅዋት ቢለያይም ጨው ጨው የማለት ባህሪ አለው። ለመጀመርያ ጊዜ ለሚቀምሰው ሰው ከበድ ሊል የሚችል የተለየ ሽታም ይኖረዋል።ብዙዎቻችን የላም ወተትን በአንድም በሌላ በደንብ እናውቃለን። ይህኛው ከዛ ቀጠን ይላል። እያደር ይኮመጥጣል እንጂ አይረጋም። ወተት ሲረጋ ቅቤ ይወጣዋል ብሎ ነገር በግመል ወተት ፉርሽ ነው። ከግመል ወተት ቅቤ ማውጣት የዋዛ አይደለም። በውስጡ የያዛቸው ንጥረ ነገሮች ወሃ ከ86-88%፣ Fat(ቅቤ) 2.9-5.4% ፣ ፕሮቲን 3.0-3.9% ፣ ስኳር(Lactose) 3.3-5.8% የተለያዩ ጠቃሚ ቫይታሚኖች እና ሚነራሎች ናቸው። በግመል ወተት ውስጥ ያለው የቅቤ መጠንን ስንመለከት አነስተኛ የሚባል አይነት ነው። በተጨማሪም ከላም ወተት ቅቤ አንጻር ስንመለከት የቅቤ ቅንጣቶቹ (Fat globules ) እጅግ ትንሽ (Size) ነው ያላቸው ይህም ለምግብ መፈጨት ስርዓቱ ቀለል ያለ እና የተመቸ ወተት ያደርገዋል። አንዳንድ ወተት የሚጣላቸው ሰዎች አሉ። Lactose intolerance! በወተት ውስጥ የሚገኘው የስኳር አይነት lactose ይሰኛል። አንዳንድ ሰዎች ሰውነታቸው lactoseን እንዲፈጭ የሚያግዝ Enzyme በበቂ ስለማያመርት ወተት በሚጠጡ ወቅት አይስማማቸውም። ጉደኛው የግመል ወተት ግን ለነዚህ ሰዎች ይመከራል። ምክንያቱም የLactose መጠኑ እጅግ አነስተኛ ነው። የግመል ወተት አጓት (whey) በውስጡ ለጤና እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እና በሽታ ተከላካይ ፕሮቲኖችን ይዞ ይገኛል። ቅጠል ተመጋቢዋ ግመል ከ1000 በላይ የተለያዩ አይነት ቅጠላቅጠሎችን በመቅጠፏ ምክንያት ወተቷ መድሀኒት አያጣውም። ለቁስል መሻያ፣ ለስኳር በሽታ ፣ ኦቲዝም እና አልዛይመር የግመል ወተት የሚበጀው ነገር አለ የሚሉ ትናቶችን ተመልክቻለሁ። በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያዊ የሚገኙት የአፋር ህዝቦች ግመል ሀብታቸው፣ መተዳደርያቸው እና የክብር መገለጫቸው ከሆኑ ህዝቦች መካከል ይገኛሉ። ከህይወታቸው ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው ግመሎቻቸውን የሚያደንቁበት፣ የሚያወድሱበት እና ስሜታቸውን የሚገልጹበት ስነ ቃል አላቸው። 'ጋሊሳሬ' ይሉታል ከብዙ መወድሶቹ መካከል ‘‘Carribar qibinah koo naxiggile Kaxxabar buxalih koonaxiggile Macakah abah mawacarriya Urrutabbixi caxah bahta meqrele’’ እንግዳ ቢመጣ በአንቺ ይስተናገዳል አባወራ እራቱን ከጡትሽ ያገኛል አንቺ እስካለሽ ድረስ በጥጋብ ይኖራል የሰው ሀብት አንቺ ነሽ ሁሉም ይመኝሻል፡፡ ግመል ጥበቃ ርቀው የተሰማሩ ወጣት ወንዶች ግመል ሳይጠጣ በፊት ውሃ አይጠጡም፡፡ ሁለት ሶስት ቀን ውሃ ተገኝቶ ባይጠጣና ቢጠሙ ወተቱን አልበው ይጠጣሉ እንጂ ውሃ ከግመሉ ቀድመው አይጠጡም፡፡ ይህም በብርታት ተፈትኖ የፅናት ባህሪውን የመውረስም ምልክት ነው። ይህ ምን ያክል በግመሎቻቸው እንደሚኮሩ አመልካች ነው። ብዙ ነገሮቻች በእጅ ያለ ወርቅ የሆኑብን አይደለን? የበረሃው ነጭ ወርቅ የግመል ወተትም በኢትዮጵያ ሀብቱ ትልቅ ቢሆንም እንደሚገባው ተጠቅመንበታል ብዬ ግን አላምንም።ለዚህ ምክንያቶቹ ብዙ ናቸው። እኛም ስለ ግመል ሀብታችን ጠቅለል ያለ መሠናዶ እያዘጋጀን ነው። ስለ ግመል ተፈጥሮ ፣ ስላለው ፋይዳ፣ ስለ ወተቱ እና እንዴት ለሀገር የሚበጅ ማድረግ እንደምንችል እንዳስሳለን። በቀጣይ ሳምንት https://t.me/campus_voice_2016 ይዚህ ይጠብቁን። ቸር ያቆየን!