የልጥፍ ይዘት
የአፍላቶክሲን ነገር! ጊዜው 2008ዓ.ም ነው። የዓለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ILRI) በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ባሉ አከባቢዎች የወተት ናሙና በመውሰድ ባደረኩት ጥናት በአውሮፓ ከተቀመጠው ልክ በላይ 'የአፍላቶክሲን' መጠን አግኝቻለሁ ሲል አሳወቀ። ILRI በወቅቱ ለ40 አመታት ያክል በኢትዮጵያ እንስሳት ሀብት ላይ ምርምር ሲያደርግ የቆየ ተቋም እንደመሆኑ ጥናቱ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ ነበር። ሰዎች በተሰራጨው ዘገባ ምክንያት የመጠጣት ፍላጎታቸው በፍርሃት ቀንሶ ወተት የሚጠጣ ሰው ሲያገኙ " ወተት አሁንም ይጠጣል እንዴ?" እያሉ ለመጠየቅ ዳርጓቸው ነበር። አስተናጋጆች ቤታቹ ምን አለ ሲባሉ የወተት ዘር መጥራት ፈርተው ነበር ፣ የወተት አምራች ኩባንያዎች በብዙ ሺ ጋሎን የሚሰፈር ወተት ደፍተው ለኪሳራም ተዳርገዋል። በወቅቱ የእንስሳት እና ዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር እና በILRI አማካኝነት በጥናቱ አዘጋገብ የተነሳ በርግጎ የነበረው የወተት ገባያ ለማረጋጋት የተለያዩ መግለጫዎች ይወጡም ነበር። የዛኔ 'አፍላቶክሲን' በኢትዮጵያ ከህፃን እስከ አዋቂ የሚያውቀውና የሚጠራው ታዋቂ ስም ሆነ። ይህ በእንስሳት ሀብትና ንግዱ ዘርፍ አወዛጋቢ ከሚባል ታሪኮች አንዱ ነው። የሆነው ሆነና አፍላቶክሲን ምንድነው? አፍላቶክሲን "አስፐርጊለት ፍሌቨስ" ፣ "አስፐርጊለስ ፓራስቲከስ" በሚባሉ የፋንገስ ዝርያዎች እና መሰሎቻቸው አማካኝነት በሚፈጠር ሻጋታ ውስጥ የሚገኝ መርዛማ ኬሚካል ነው። ሻጋታ የሚፈጠረው ምርት እርጥበቱ ሳይጠፋ በሚከማችበት ጊዜ አልያም ኬሚካሉን አመንጪ የሆኑት ፋንገሶች "ስፖር" እህሎች በሚዘሩበት እርሻ ውስጥ ተሰራጭቶ ሲገኝ ነው። ሞቃታማና እርጥበት አዘል በሆኑ የዓለም አከባቢዎች በተለይ ከሰሃራ በታች በሚገኙ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ውስጥ በሚመረቱ እህል ዓይነቶች ውስጥ አፍላቶክሲን በብዛት ይገኛል። ቅርፊት ያላቸው እንደ በቆሎና ለውዝ ያሉ የእህል ዘሮች በእርጥበታማ ቦታዎች በሚከማቹበት ጊዜ በቅርፊታቸው እርጥበት የመያዝ ባህሪ ስላላቸው የመሻገት ዕድላቸው የሰፋ ነው። ለውዝ፣ በቆሎ፣ የጥጥ ፍሬ ፣ ቦሎቄ ፣ በርበሬ ፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ወዘተ በምርት ክምችት ወቅት በሚፈጠር ስህተት ምክንያት አፍላቶክሲን በከፍተኛ መጠን ሊገኝባቸው ይችላል። በተጨማሪም የእንስሳት መኖዎች በእርጥበታማ አከባቢ ሲከማቹ እና ሳይሌጅ በሚዘጋጅበት ወቅት ነፋስ እና እርጥበት በሚያገኝበት ሁኔታ ከተቀመጠ በቀላሉ ሻጋታ ሊሰራ እና አፍላቶክሲን በመኖ ውስጥ ሊገኝ ይችላል። የአለም የእህል ምርት 25% በአፍላቶክሲን ይበከላል። አፍሪካም ባላት አየር ጠባይ ሳብያ 80% የሚሆኑ ሕዝቦቿ ለአፍላቶክሲን ጉዳት የተጋለጡ መሆናቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። በአንድ ሀገር ውስጥ በእንስሳት መኖዎች እና በሰዎች በተለይ በህፃናት ምግብ ውስጥ የሚገኘው አፍላቶክሲን ቁጥጥር የማይደረግበት ከሆነ እና የምርት አከመቻቸት ዘዴው አፍላቶክሲንን ያላማከለ ከሆነ በዋናነት ሁለት መሠረታዊ ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። የጤና መታወክ እና የኤክስፖርት ንግድ መቀነስ! አፍላቶክሲን ወደ ሰውነት እንደገባ "ሜታቦላይዝ" የሚደረገው በጉበት ነው። ለብዙ ጊዜ በከፍተኛ መጠን ለዚህ ኬሚካል ጉበት ተጋላጭ ሲሆን የጉበት ካንሰር ሊያስከትል ይችላል። B1 ፣ B2 ፣ G1 ፣ G2 የሚባሉ ሰብሎች ላይ የሚገኙ እና M1፣ M2 የሚባሉ እንስሳት እጽዋቶቹን ከተመገቡ በኋላ "ሜታቦላይዝ" በማድረግ የሚፈጥሯቸው የአፍላቶክሲን አይነቶች አሉ። B1 የጨጓረሠ ካንሰር ሊያስከትል የሚችል ነው። M1 የሚባለውም መጠኑ በእንስሳት ተዋጽኦ ውስጥ እጅግ ከፍ ሲል መርዛማ ነው። በተጨማሪም አፍላቶክሲን የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅምን ይቀንሳል። በህፃናት ላይ የእድገት ውስንነት፣ የጉበት በሽታ፣ ከፍተኛ የሆነ የበሽታ ተጋላጭነት እና ለካንሰር የመጠቃት እድል ከፍተኛ መሆን ሊያስከትል ይችላል። አፍላቶክሲን በከፍተኛ መጠን በመኖዋቸው ውስጥ የሚገኝ እንስሳትም የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ምርት እና እድገት ማሽቆልቆል፣ በበሽታ ቶሎ ቶሎ የመጠቃት ነገር ሊስተዋልባቸው ይችላል። እንደ ወተት ባለ ተዋጽዋቸው ውስጥም ኬሚካሉ ይኖራል። ይህንን መጠነ ሰፊ የጤና ጉዳት ለመከላከል ታድያ የተለያዩ ሀገራት በተለይ ያደጉ የምንላቸው በምግብ ምርት ውስጥ መገኘት ያለበትን የአፍላቶክሲን መጠን ወስነዋል። በርግጥ አፍላቶክሲን በውስጡ የሌለ ምግብ ማለት የሚቻል ባይሆንም አውሮፓ ከ0.05ug/kg በላይ የሆነ አፍላቶክሲን ያለበት ምግብ መርዛማ ነው ትላለች። አሜሪካም ከ0.5ug/kg በላይ የሆነ አፍላቶክሲን የሚገኝበት ምግብ በገበታ ላይ እንዲኖር አትፈቅድም። ለዚህም ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር ወደ ሀገራቸው በሚገቡ ምግቦች ላይ ያደርጋሉ። ሀገራት ይህን መስፈርት የሚያወጡበት የተለያዩ መንገዶች ይኖሯቸውዋል። ሀገራችንም ካለችበት ደረጃ ጋር በማመዛዘን ከ2008ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ኤጄንሲ አማካኝነት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የምግብ ውጤቶች ልኬት የምታደርግ ሲሆን ከ5ug/kg በላይ የB1 አፍላቶክሲን የሚገኝበት ምርት ጥቅም ላይ እንዲውል አይፈቀድም። ለህፃናት ምግብ ደግሞ መጠኑ እስከ 2ug/kg ዝቅ ይላል። ከላይ ከዘረዘርኳቸው ነገሮች እንደምንረዳው አንድ ሀገር ወደ ሌላኛው ሀገር የምግብ ውጤቶችን ኤክስፖርት ማድረግ ሲፈልግ የተቀባዩን ሀገር የአፍላቶክሲን ገደብ ማወቅና ማክበር አለበት። ለዚህም በቂ ቁጥጥር እና ህግ በማይኖር ከሆነ የኤክስፖርት ንግዱ እለት እለት ማሽቆልቆሉ የማይቀር ነው። የቅርብ የሆነ መረጃ ባይኖረኝም በተለይ ወደ እንግሊዝ ሀገር በኮንቴነር ሳይቀር የተላኩ በሺ ቶን የሚለኩ ቅመማ ቅመሞች በዚሁ አፍላቶክሲን ጣጣ ወደ ኋላ ተቋጥረው እኖዲመለሱ ተደርገዋል። መገኘት የነበረበትም የውጪ ምንዛሪ ወሃ በልቶታል። እንደ ኢትዮጵያ ላለች የውጪ ምንዛሪዋ በግብርና ውጤቶች ላይ ለተንተራሰ ሀገር ይሄ ቀልድ አይደለም። ይልቅ አንድ ሌላ አንድ ቀልድ አውቃለሁ፤ ሰውዬው ርቦት ቤቱ ገባ፣ የጓዳውን ፋኖስ አብርቶ ቢያይ ከመሶቡ ከአንዲት ስትበላ የተረፈች ሻጋታ ዳቦ በቀር አንዳች አልነበረም። ሰውዬው የሆዱን ጥያቄ አልቻለም እና የሻገተ በላህ የሚለውን የአእምሮ ጥያቄ ለመሸሽ ሲል ዳቦዋን ፋኖሱን አጥፍቶ በላት። አፍላቶክሲን የዋዛ አይደለም ለሚነገሩን ሳይንሳዊ እውነቶች መብራታችንን እያጠፋን ደጋግመን ብንበላው ነገ በሽታ ሆኖ ይመጣል። ጉዳዩ ብዙ የሚባልበት ቢሆንም እኔ እዚህ ጋር ላብቃ። በቀጣይ ከቻልኩ ሻጋታ የሚፈጠርበትን ባህላዊ የምግብ አከማቸታንን ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ከላይ ያለውን ሀሳብ ያጠናከርኩላችሁ የተለያዩ ጥናቶችን በማንበብ እና በተለይ ሮይተርስ በተለያዩ ጊዜያት ስለ አፍላቶክሲን ያወጣቸውን መረጃዎች በመዳሰስ ነው። በዘርፉ ጥናት ያደረጋችሁ ሰዎች ደግሞ ወቅታዊ የአፍላቶክሲን መረጃዎችን ጀባ ብትሉን ደስታዬ ነው። ለታጋሽ ንባባችሁ አመስጋኝ ነኝ! ቸር ያቆየን!!