የልጥፍ ይዘት
ትዝ ብሎኝ እኮ ነው! ቡሄን በእንግሊዝኛ ለህንዳውያን ለማስረዳት የሞከርኩ ሰው ነኝ። አሁን ሳስበው ሙከራው ውርጭን በካኒቴራ በረሃን በብርድ ልብስ ለመጓዝ የመድፈር ያክል ነበር። አስቡት ቡሄን ያክል ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትውፊት የህንድ እውቅያኖስን ተሻግሬ የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚነገሩባት ህንድ ነዋሪ ሳብራራ። ዝም ብላችሁ አስቡት.... ወዲህ በአማረኛ እያሰበ ወደ እንግሊዝኛ ተርጉሞ የሚያወራ የኔ "ሜዱላ" አለ። ወዲያ የኢትዮጵያ ባህል በወሬ ካልሆነ አይተው የማያውቁ በእንግሊዝኛ ሰምተው ህንድ ውስጥ ካሉ ቋንቋዎች በአንዱ የሚረዱ እነርሱ አሉ። ልገነባ ያሰብኩት ድልድይ ቋንቋን ፣ ባህልን ፣ ስነ ልቦናን እና ሐይማኖትን ተሻግሮ በሀሳብ ተግባብተን ጭንቅላታችንን እንድንነቀንቅ ሊያደርግ የጠነከረ መሆን ይገባዋል። ይህን ድልድይ በጥቂት እውቀት ለመገንባት መሞከር በርግጥ እብደት ይመስላል። ...But we did it በዘነዘና😅 ነገሩ እንዲህ ነው። መቼም ሮትራክትን ታውቃላችሁ?! የሮትራክት ኩሪፍቱ ክበብ አባል ነኝ። በሮትራክት ክለቦች ውስጥ ደግሞ International Relationship የምንለው ነገር አለ። በአጭሩ ሲገለጽ ክለቦች ከሌላ ሀገር አቻዎቻቸው ጋር ልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት እና የጋራ ስራ የሚሰሩበት አይነት ነው።በክለቡ ውስጥ ይህን የሚመራ የራሱ ዳይሬክተር ይኖረዋል። የኛ ዳይሬክተር ሜቲ ትባላለች። ሜቲ ህንድ ሀገር ከሚገኝ ሮትራክት ክለብ ጋር የ online Cultural exchange event ለማዘጋጀት እየተጻጻፈች እንደሆነ ነገረችን። ይበጅሽ "ቲኬ ሜትሪና" አልናት። ሜቲ ኦሮምኛ ቢሆንም ካትሪና የሚባል የህንድ ስም እናውቃለን እና ህንዳዊ ለዛ አስያዝነው። በየስብሰባችን ስለ Eventኡ እንድትነገረን ስንፈልግ "ናማስቴ ሜትሪና ያ ነገር ከምን ደረሰ?" እንል ነበር። ትንሽ ሳቅ ይፈጥራል። ቀኑ ከይደርስ መስሎን! ይህ ሁሉ ሲሆን ባህላችንን የሚያስተዋውቀው ማን እንደሆነ ገና አላወቅንም ነበር። ኸረ ጉዴን አላወኩም ነበር ብል ይቀለኛል! ለማቅረብ ቀናት ሲቀሩን ጉዴ ተነገረኝ። "አንተ ነህ ምታቀርበው" ተባልኩ! በሻሩክ ሞት! አልዋሻችሁም ጨነቀኝ። ወላ ጠበበኝ። ስለማቀርበው ነገር ሳስብ ቀኑ ቶሎ ያልቅብኛል። " 'ራት ሰዓት ላይ አሁን አይደል ምሳ የበላሁት?" እላለሁ። ጠዋት ስነሳ ከምኔው ነጋ እላለሁ። የአንስታይን ሰራተኛ እውነቷን ነው። ስለ ጊዜ ሲጠይቃት ከፍቅረኛዬ ጋር የተቀጣጠርኩ ጊዜ ሰዓቱ ለመድረረስ ዘላለም ነው ፣ ከተገናኘን በኋላ ደግሞ የዘገየውን ሊያካክስ ነው መሠል ሽምጥ ይጋልባል ያለችው። እኔ ቀጠሮዬ ከፍቅረኛዬ ጋር አይደለም። በምን እድሌ! ለኔ ሰአቱ ከጭንቅ ቀኔ ለማድረስ ነው ሽምጥ የጋለበብኝ። በተቻለኝ አቅም ስለ ቡሄ ለማንበብ ከልጅነቴ ለማስታወስ ሞከርኩ። ጭራሽ ለማወቅ በጣርኩ ቁጥር ቡሄ የማላውቀው አንዲስ በዓል ሆኖ ቁጭ አለ። ትውፊቱ ፣ አንድምታው ለኔ በየአመቱ እየጠበኩ ለማከብረው ደነቀኝ። እንደ አዲስ የገረመኝ ነገር ነው እንግዲህ ቋንቋ ቀይሬ ማቀርበው! ሲፈጥረኝ መድረክ ሁሌ አዲስ ይሆንብኛል። የሚያደምጠኝ እንዲሰላች አልፈልግም። የታዳሚው ብዛት ምንም ይሁን ምን ሰአቱን ሰውቶ መገኘቱን አከብራለሁ። ቢቻል ቢቻል ከመድረኩ አዲስ ነገር ማግኘት አለበት። አልያ ደግሞ ከዚህ በፊት የሚያውቃቸው ነገሮች እንኳ በአዲስ እይታ ተቃኝቶ እንዲያገኘው እፈልጋለሁ። በእኔ እምነት የመድረክ ሰው ግብሩ ቡና መሆን ነው። ታዳሚ ንቅት ብሎ ሀሳብ ወደ ምዕናቡ እንዲፈስ ማድረግ። ምንም እንኳ ይህ የonline መድረክ ቢሆንም(ነገር በአይን ይገባል ባይባልለት) ዝግጅቱ የማይሰለች ለዛ እንዲኖረው ፈልግያለሁ። ስለዚህ እንደ መግብያ ህንድ እና ኢትዮጵያን የሚያጋራ ነገር ማውራት ፈለኩ። እኔ እና አንድ የህንድ ወጣት ምን የጋራ ነገር አለን? ምን አይነት ተመሣሣይ ልጅነት ነበረን? አብረን ጭቃ አብክተናል? ቴዘር እነርሱ ጋር ይኖር ይሆን? እሺ መሃረቤን አያችሁ ወይ ተጫውተዋል? ለህንድ ህፃን ከማር ከወተት መጓተት ይሻላል? አሃ! አንድ ነገር አለ! ሻሩክ ካን። ያ የህንዱ የፍቅር ተምሳሌት። Bollywood! በቃ ስለ Bollywood አወራለሁ! ልጅነቴ ውስጥ ምን አይነት ተጽእኖ እንደነበረው አንዳንድ ቃላትን ከፊልም ከሰማሁት እየቀላቀልኩ እነግራቸዋለሁ። እንደሚወዱት እርግጠኛ ነበርኩ። ሻሩክ የእነሱም የእኛም ልጅነት ውስጥ አለ! የለቱ ለተ የሮትራክት ኩሪፍቱ አባላት በአሉን ከአንድ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል በጋራ ነበር ያከበርነው። ሜትሪና እነሱ በጣም ጠዋት ሳይሆንባቸው፣ እኛም ጋር ጸሐይ ሳትጠልቅ የሚያገናኘን አመቺ ነው ባልችበት ሰዓት ከአንድ ሆቴል ገብተን ተሰናዳን። ሲነበቡ የሚያኮላትፉ ስም ያለቸው ሰዎች የውውይት ሊንኩን Join ማድረግ ጀመሩ። የሞነጫጨርኩበትን ወረቀት አወጣሁ። ራሳችንን አስተዋወቅን። የተዘጋጀሁበትን በድሮን ዘመን ቆመጠብቀኝን የመሠለ እንግሊዝኛ ማቅረብ ተያያዝኩ። አንዳንድ ቃላት በቃ መገለጽ ሚችሉት በአንድ ቋንቋ ብቻ ነው።ከንድ አረፍተ ነገር ጨርሼ ቆም እላለሁ። ይጠብቁኛል። ስለ ሻሩክ በተመስጦ አወራሁ እናንተ ህንዶች በBollywood ብዙ ነገር ነግራችሁናል አልኩ።የ bollywoodን አለማቀፋዊነት አደነኩ። ስለ ቡሄ ተረኩ። በአሉን ስናከብር የሚያሳዩ ቪዲዎች አጋራናቸው። ተገላገልኩ! ተራቸው ደረሰ ያቀረብነውን ባህል ወደውታል። ስለ ላሊበላና እና እና አክሱም ያወራነው የእነሱን የ Architecture ስልጣኔ እንዲያወሩን ገፋፍቷቸዋል። ግን አንድ ነገር ደስ አላላቸውም። ግዙፉን የህንድ ፊልም industry በ Bollywood ብቻ ነው የጠቀለልከው አሉኝ። Bollywood ሙምባይ ላይ የተመሠረተ የተወሰነ ህንድ ክፍልን ባህል የሚያሳይ እንጁ የሙሉ ህንድ ገጽታ መገለጫ እንዳልሆነ ነገሩኝ። በ Hyderabed እና Kolkata የሚገኘውን Tollywood የChannaiን Kollywood ረስተሃል አሉኝ። እንዳጋጣሚ ታዳሚዎቻችን ከChennai ነበሩ። የምር በጣም ነበር የደነገጥኩት። ማጥናት ነበረብኝ። ስለ ፊልም industryያቸው በወፍ በረር ከማውቀው በተጨማሪ ማንበብ ነበረብኝ። የዲፕሎማሲ አንዱ ምሰሶ የራስን ብቻ ሳይሆን የሌላን ሀገር ባህል እና ስነ ልቦና ማወቅ ነው። የምንለውን የሚረዱበትን አውድ መገንዘብ። የነገሩን መረጃ በጣም እንዳስደመመኝ እና ስለ ፊልም Industryያቸው አድማስ በደንብ እንደማጠና ቃል ገባሁላቸው እና ተለያየን። ያ ቀን ትልቅ ትምህርት የወሰድኩበት ነው! ከመጻፍም ሆነ ከማውራቴ በፊት በቂ መረጃ እንዳለኝ እንድፈትሽ አድርገጎኛል። Rotaract አይደል ክለቤ! ከስህተቴ ከተማርኩባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አንዱ ሆኖ አልፏል። ይህን ሁሉ የጻፍኩት እንግዲህ እኔ ወንድማችሁ ቡሄን በእንግሊዘኛ ለህንዳውያን ያቀረብኩ ሰው ብዬ ለመጎረረር ነው😂 ቸር ያቆየን!