@ebcnewsnow · Post #51928 · 26.02.2026 г., 09:57
የሦስቱን ዞኖች ትስስር የሚያጠናክረው የ97 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ግንባታ *************** በጉራጌ፣ ስልጤ እና ሀዲያ ዞኖች መካከል ያለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ የሚያሳልጠው የአጣጥ ማዞሪያ - ጉንችሬ - ቆሴ - ሌራ - ጌጃ የአስፋልት መንገድ ግንባታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ነው። በፌደራል መንግሥት በ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በጀት እየተገነባ የሚገኘው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ እስካሁን 56 በመቶ የሚሆነው ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከጠቅላላው 97 ኪሎ ሜትር ውስጥ 49 ኪሎ ሜትሩ የአስፋልት ንጣፍ ተደርጎለታል። ዓለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ እያከናወነው የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ በጉራጌ ዞን የቸሃ፣ የእኖር፣ የእኖር ኤነርና መገር እንዲሁም እንደጋኝ ወረዳዎችን፣ በሀዲያ ዞን የአመካ ወረዳን እና በስልጤ ዞን የምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳዎችን በዋናነት ተጠቃሚ ያደርጋል። አሁን ላይ የመሬት ጠረጋ፣ የውኃ ማፋሰሻ ቱቦ፣ የአፈር ቆረጣና ሙሌት እንዲሁም ሌሎች የስትራክቸር ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወኑ ይገኛሉ። አካታች የሆነ የልማት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠው ይህ የመንገድ ግንባታ፣ በቀጣዩ ዓመት 2019 ሰኔ ወር ላይ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ይጠበቃል። በአስማረ ብርሀኑ #EBC#Ethiopia#Infrastructure#RoadConstruction#Gurage#Siltie#Hadiya#DevelopmentNews