@borkena · Post #5884 · 27.02.2026 г., 16:33
በቆቦ ገበያ ላይ ቢያንስ 5 ንፁሃን በሚሊሺያ ተገደሉ። ጥቃቱን የፈፀሙት የሚሊሺያ ሀይሎች መሆናቸውን የአይን አማኞች ለቦርከና አረጋግጠዋል። ሚሊሺያዎቹ ጥቃቱን የፈፀሙት የፋኖ ሀይሎች በሚሊሺያ ካምፕ ላይ በወሰዱት እርምጃ አንድ ከፍተኛ አመራራቸው ከነ አጃቢዎቹ በመገደሉ መሆናቸውን ገልፀዋል። በአካባቢው የነበረ አንድ የአይን እማኝ "ሰው በየቦታው ነው የሞተው፣ ቢያንስ አምስት ሰዎች በጭካኔ ተመትተው ወድቀዋል" ሲል የተመለከተውን ገልጿል። "አንዱ ሟች ከወልዲያ ከተማ ነው የሄደው፣ ጉሊት በመሸጥ ነበር የሚተዳደረው፣ ቁጭ ብሎ ከሚሸጥበት ነው በሚሊሺያ ሀይሎች የተገደለው" ሲል ስለ ክስተቱ አስረድቷል። እኒሁ የቦርከና ምንጭ "ሰው ጥቃቱ ሲፈፀም ደንግጦ ተበታትኗል፣ ተኩስ የተፈፀመው ገበያ ላይ ስለሆነ የሟቾቹ ቁጥራቸው ብዙ ነው የሚሆነው" ብሏል። የተወሰኑት ሟቾች አስክሬን ለቤተሰብ መላኩን ገልፀዋል።ጥቃት አድራሾቹ ከአካባቢው በመሰወራቸው የመንግስት ሚሊሺያዎች ህዝቡ ላይ ተኩሰዋል ሲሉ የተመለከቱትን አስረድተዋል። በቆቦ ገበያ ሁልጊዜ ሰኞ እና አርብ ትልቅ ገበያ እንደሚካሄድ የመረጃ ምንጩ ተናግረዋል። ነገርግን ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተከሰተው ግጭት እና የፀጥታ መደፍረስ አካባቢው የተረጋጋ እንዳይሆን ማድረጉ ተመላክቷል። #Ethiopia#Amhara#Kobo#Ethiopian_news#ዜና#ቆቦ