@borkena · Post #6005 · 03/13/2026, 03:10 PM
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ኢትዮጵያ በማንኛውም መንገድ የባሕር በር ባለቤት መሆን አለባት አሉ። ኢትዮጵያ በማንኛውም መንገድ የባሕር በር ባለቤት መሆን አለባት ሲሉ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ተናግረዋል። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የበለጠ አስተማማኝና ውጤታማ መሆን የሚችለው ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር ሲኖራት ነው ብለዋል። የባሕር በር ጥያቄው ቢቻል ሰላማዊ በሆነ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ጠቅሰው፤ ካልተቻለ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ሳታገኝ ታፍና መኖር እንደማትችል ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በማንኛውም መንገድ የባሕር በር ባለቤት መሆን አለባት ሲሉ መናገራቸውን ኢፒድ ዘግቧል። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የራሴ የምትለው የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት የተናገሩት ሙላቱ፤ የሀገሪቱ ብልጽግና እውን መሆን የሚችለው ያመረተችውን ምርት በራሷ በር ስታስወጣና ስታስገባ መሆኑን አስገንዝበዋል። ሙላቱ የባሕር በር የምንለምነው መሆን የለበትም፤ የእኛ የነበረ ነው ያሉ ሲሆን ጥያቄው በማይሆን ሁኔታ ከእጃችን ያመለጠው የባሕር በር ወደ ራሳችን ይመለስልን የሚል መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ የሌላውን ሀገር መሬት የመውሰድ ፍላጎት እንደሌላት ጠቅሰው፤ ለህልውናዋ ግን የባሕር በር የግድ እንደሚያስፈልጋት ገልፀዋል። #Ethiopia#AddisAbaba#Redsead#Port#ሙላቱ_ተሾመ#ቀይ_ባህር#ወደብ#ኤርትራ#ዜና#ቦርከና_ዜና