@ebcnewsnow · Post #53458 · 04/13/2026, 03:30 PM
የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ያለፉ ሰዓታት ሁኔታ፦ የሰላም ጥረቶች መሰናከል እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ ************** በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ወታደራዊ ውጥረት ዛሬ ወደ አዲስ እና አደገኛ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። በፓኪስታን፣ ኢስላማባድ ለ21 ሰዓታት የተካሄደው የሰላም ድርድር ያለምንም ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) ዛሬ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢራን ወደቦች ላይ መደበኛ የባሕር ከበባ መጀመሩን አስታውቋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የምታስከፍለውን ክፍያ “ዓለም አቀፍ ዝርፊያ” ሲሉ በመኮነን፣ ክፍያውን የሚፈጽም ማንኛውም መርከብ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር እንደሚውል አስጠንቅቀዋል። በሌላ በኩል፣ ኢራን ሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሯ ሥር መሆኑን በመግለጽ፣ የባሕር ከበባውን እንደማትቀበልና ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ ከባድ አጸፋዊ ምላሽ እንደሚያስከትል አሳውቃለች። እንግሊዝ እና ፈረንሳይ የአሜሪካን የባሕር ከበባ እንደማይደግፉ በማስታወቅ፣ ከጦርነቱ ተሳታፊዎች ነጻ የሆነ እና ጥብቅ የመከላከል ዓላማ ያለው ሰላማዊ ዓለም አቀፍ የባሕር ኃይል ጥምረት ለማቋቋም የጋራ ጉባኤ ጠርተዋል። ቻይና እና ሩስያ መፍትሔው ወታደራዊ ኃይል ሳይሆን በአስቸኳይ ተኩስ አቁም ላይ መድረስ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ከበባው የዓለም አቀፍ ንግድ መስመርን እንደሚያስተጓጉል አስጠንቅቀዋል። ሳውዲ ዓረቢያ ከደኅንነት ስትራቴጂ አኳያ ጥንቃቄ የተሞላበት ዝምታን ስትመርጥ፣ ኳታር ቀጣናው ከቁጥጥር ውጪ ወደሆነ ጦርነት እያመራ ነው በማለት ስጋቷን ገልጻለች። ፓኪስታን እና ኦማን በበኩላቸው የተጀመረውን የሽምግልና ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሲያረጋግጡ፣ እስራኤል የአሜሪካን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ደግፋለች። እንደ ዎል ስትሪት ጆርናል እና ሌሎች ሁነኛ የመረጃ ምንጮች፣ በኢስላማባድ የተካሄደው የሰላም ድርድር ላለመሳካቱ ዋናው ምክንያት የኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር እና የሆርሙዝ ወሽመጥ የቁጥጥር ሥልጣን ጉዳይ ነው። የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ኢራን የኑክሌር ፍላጎቷን እንድታቆም ያቀረቡትን ጥያቄ አለመቀበሏን ሲገልጹ፤ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ በበኩላቸው የአሜሪካ ከፍተኛ ጫና እና የከበባ ዛቻ ለስምምነት ተቃርቦ የነበረውን ድርድር እንዳደናቀፈው ገልጸዋል። የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተንታኞች የቀጣዩን ጊዜ ሁኔታ በከፍተኛ ስጋት እየተመለከቱት ነው። የስትራቴጂያዊ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል (CSIS) ተንታኞች እንደሚሉት፣ ይህ ጫና ኢራን በየመን የሚገኙ የሁቲ ኃይሎችን በመጠቀም በባቢል መንደብ ወሽመጥ ላይ ተጨማሪ ጥቃቶች እንድትሰነዝር ሊገፋት ይችላል። ይህ ከሆነ እና በአንድ ጊዜ ሁለት ዋና ዋና የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮች ከተዘጉ፣ ከ100 ዶላር በላይ የዘለለው የነዳጅ ዋጋ እስከ 150 ዶላር ሊያሻቅብ እንደሚችል የገበያ ተንታኞች ይገምታሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በበኩሉ፣ ጦርነቱ እና የኢኮኖሚ መናጋቱ በዓለም ዙሪያ 32 ሚሊዮን ሰዎችን ወደ ድህነት ሊገፋ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል። ከነዚህ አስተያየቶች በመነሳት የተጀመረው የሰላም ጥረት እና የኦማን የሽምግልና ሚና አሁንም ብቸኛው የቀውሱ መውጫ ተስፋ ተደርጎ እየታየ ይገኛል። ለሚ ታደሰ #MiddleEastCrisis#StraitOfHormuz#NavalBlockade#EnergySecurity#Diplomacy