@ebcnewsnow · Post #54038 · 25.04.2026 г., 18:53
ሀዋሳ በአፍሪካ ትልቁን የሶላር ሴል ምርት የምታመርት ከተማ ሆናለች - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ************ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነቡትን የቶዮ ሶላር ኢነርጂ ምዕራፍ 2፣ የኦሪጂን እና የሉሚንቴክ የሶላር ፋብሪካዎችን እንዲሁም የኤች.ዜድ ጋዝ ማምረቻ ፋብሪካን በይፋ መርቀዋል። ሦስቱ የሶላር ፋብሪካዎች በዓመት በድምሩ 11.3 ጊጋ ዋት ንጹሕ ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን፣ የኤች.ዜድ ጋዝ ፋብሪካ ደግሞ በዓመት 900 ቶን ኦክስጅን፣ 40 ሺህ ቶን ናይትሮጅን እና 7 ቶን ሃይድሮጅን ለገበያ የሚያቀርብ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ከዚህ ቀደም ሰዎች ወደ ሀዋሳ የሚመጡበት ዋናው ምክንያት በከተማዋ ውበት እና መስተንግዶ ለመደሰት እና ለመዝናናት እንደነበር አንስተዋል። አክለውም፥ አሁን ደግሞ ሀዋሳ በቀድሞ ታሪኳ ላይ ሌላ አዲስ ታሪክ በማከል በአፍሪካ ትልቁ የሶላር ሴል ምርት የሚመረትባት ከተማ መሆን መቻሏን በመጥቀስ የከተማዋን ነዋሪዎች “እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋቸዋል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨርቃጨርቅ ይመረትበት እንደነበረ ጠቅሰው፣ በዚህ መሃል የአጎዋ የቀረጥ ነፃ ኤክስፖርት ዕድል በመቋረጡ 90 በመቶ ሼዶች ሥራ ፈትተው ፓርኩን ለቀው መውጣታቸውን አስታውሰዋል። ከክስተቱ አካሄዳችን አያዋጣም፣ ምርት ማስፋት (ዳይቨርሲፋይ ማድረግ) አለብን፣ በአንድ ዘርፍ እና በአንድ ገበያ ላይ ብቻ የተመሠረተ አካሄድ ለኢትዮጵያ አያዋጣም የሚል ትምህርት ወስደናል ብለዋል። ከዚያም ከዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ወደ ቬትናም በመሄድ በሶላር ዘርፍ ተለቅ ያለ ገንዘብ ኢንቬስት አድርገው በቀላሉ ገበያ ማምጣት ለሚችሉ ባለሃብቶች ግብዣ አቅርበናል ነው ያሉት። በወቅቱ በቬትናም ቶዮን ጎብኝተን፣ እንደዚያ ያለ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ ለማየት በጣም ጓጉተን ነበር፤ ቶዮ መጥቶ የመጀመሪያውን ፌዝ 2 ጊጋ ዋት ሥራ ካስጀመረ በኋላ ወደ 4 ጊጋ ዋት ለማሳደግ ወሰነ፤ ሌሎች ሁለት ተጨማሪ ፋብሪካዎችም እርሱን ተከትለው በመምጣታቸው አሁን የፓርኩ ዓመታዊ አማካይ የማምረት አቅም 11.3 ጊጋ ዋት ደርሷል ሲሉ አብራርተዋል። #Hawassa#SolarPanel#Factories#AbiyAhmed#EBC