@ebcnewsnow · Post #52687 · 25.03.2026 г., 02:59
የሰው ልጅ አሁን በደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ ከተሞች እጅግ ዘምነዋል። ለኑሮ፣ ለምርታማነትና ዕምቅ ዐቅማቸውን ለመጠቀም በሚያስችላቸው መልኩ ተደራጅተዋል። በጋራ ሠልጥኖ ለመኖር ሥርዓትና ኃይል የተደራጀባቸው ተመራጭና ተቀዳሚ ቦታዎች ሆነዋል። ከተሜነት የሰው ልጅ የብልጽግና መዳረሻ ነው ብንል ገሐዳዊውን ዓለም ምስከራችን አድርገን ነው። ከተሞች ለሰው ልጅ አካላዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ጤንነቱ ተጠብቆ አምራችነቱ እንዲያድግ ማኅበራዊ መስተጋብሩን ይፈጥሩለታል። ድካሙን ቀንሶ ትርፍ ለማምረት የሚያስችሉ የግብአትና የክሂሎት አቅርቦትና ተደጋጋፊነት በከተሞች ይገኛል። እነዚህ ሁሉ የሰውን ልጅ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መሻቶች ለማሳካት ያስችሉታል። እንዲሁም በተፈጥሮ የተሰጠውን የመመራመርና የመጠየቅ ስጦታ ተጠቅሞ አዳዲስ ፈጠራዎችንና ሐሳቦችን ለማፍለቅ ከተሞች አስቻይ ዐቅም ሆነውታል። የመደመር አንቀፅ ገፅ 223 Ethiopian Broadcasting Corporation #PMAbiyAhmed#Ethiopia#Addis
Hashtags