@ebcnewsnow · Post #51323 · 28.01.2026 г., 13:46
"በስማችሁ ገንዘብ ተጠይቆባችሁ ያውቃል? ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ለሳይበር ሌቦች ሰለባ እንዳይሆኑ ይህንን የጥንቃቄ መልዕክት ያጋሩላቸው!" *********************** በኢትዮጵያ በዋትሳፕ (WhatsApp)፣ በቴሌግራም (Telegram) እና በሌሎች የመልዕክት መላላኪያ ማህበራዊ ገጾች አማካኝነት የሚፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች እና የማጭበርበር ድርጊቶች በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመራቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ። ወንጀለኞቹ ወቅታዊ ኩነቶችን፣ ሲምፖዚየሞችን እና ስብሰባዎችን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን እንደሚጠቀሙ አስተዳደሩ ገልጿል። ከማጭበርበሪያ ስልቶቹ መካከልም "ነጻ የኢንተርኔት ፓኬጅ" እና "ልዩ የሥራ ቅጥር" የሚሉ አሳሳች መልዕክቶችን ማሰራጨት አንዱ መሆኑን ገልጿል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ተጠቃሚዎች በመልዕክቱ ውስጥ ያሉ ሊንኮችን (Links) እንዲጫኑ በማድረግ አካውንታቸውን መጥለፍ ነው። በሦስተኛ ደረጃ የተጠለፈውን አካውንት በመጠቀም በተጎጂው ስም ከቅርብ ዘመዶቹ የገንዘብ ድጋፍ መጠየቅ መሆናቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ባወጣው መረጃ አስታውቋል። እንዲህ አይነት ክስተቶችን ለመከላከል እና ተጎጂ ላለመሆን ማህበረሰቡ ከሳይበር ጥቃት ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ያሳሰበው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በተለይ የሚከተሉትን መውሰድ እነደሚገባ በጥብቅ አሳስቧል፦ 1. አጠራጣሪ ሊንኮችን አለመክፈት፡ ከማይታወቁ አድራሻዎች የሚላኩ መልዕክቶችን "Report" እና "Block" ማድረግ። 2. ምስጢራዊ ኮዶችን አለመስጠት፡ በስልክ የሚላክ የማረጋገጫ ኮድን (Verification Code) ለማንም አካል አለመንገር። 3. የሁለትዮሽ ማረጋገጫ (Two-Step Verification)፡ ጠላፊዎች በቀላሉ አካውንትን እንዳይቆጣጠሩ ተጨማሪ የደህንነት ቁልፍ የሚፈጥረውን የቴክኖሎጂ ዘዴ በአስቸኳይ መተግበር። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ወንጀለኞችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጾ፣ ማንኛውም አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ሲያጋጥም በነጻ ስልክ መስመር 933 በመደወል ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል። #EthiopianBroadcastingCorporation#Verification#ኢመደአ