@ebcnewsnow · Post #51344 · 29.01.2026 г., 11:39
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ብራንድ አምባሳደር ሆነ ************** የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም በአትሌቲክስ በተለያዩ ርቀቶች የዓለም ሪከርድ ባለቤት የሆነውን አትሌት ቀነኒሳ በቀለን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ብራንድ አምባሳደር አድርጓል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ብራንድ አምባሳደር ሆኖ የተሰየመው፣ ብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የፋይዳ አምባሳደር ይፋዊ ሥራ ማስጀመሪያ መርኃ ግብርን ባካሄደበት ወቅት ነው። የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ፋይዳን ለሁሉም ለማድረስ የ100 ፐርሰንት ዕቅድ አቅዷል፡፡ እስካሁን ከ32 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የመታወቂያው ባለቤት መሆናቸውና በበጀት ዓመቱም ለ 90 ሚሊዮን ዜጎች ለማድረስ ዕቅድ መያዙ ተገልጿል። ይህን ግብ ለመደገፍም ታዋቂ እና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የብራንድ አምባሳደር መሰየም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ አትሌት ቀነኒሳን ብራንድ አምባሳደር ማድረጋቸውን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና አስተባባሪ አቶ ዮዳሄ አርዓያስላሴ ተናግረዋል። አቶ ዮዳሄ አክለውም፤ አትሌቱ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እና ተወዳጅነት በመጠቀም በሁሉም የሀገሪቱ ከፍሎች ያሉ ነዋሪዎችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንደሚሰራም ገልጸዋል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ፤ ሀገራዊ ፋይዳ ላለው ፕሮጀከት ብራንድ አምባሳደር ሆኖ በመመረጡ ክብር እንደሚሰማው ተናግሯል። የፋይዳ አምባሳደር አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፤ በአምባሳደርነት ቆይታው የተለያዩ የቴለቪዥን፣ የማህበራዊ ሚዲያ፣ የቢልቦርድ ማስታወቂያዎች ላይ መሳተፍ እንዲሁም የተለያዩ ኩነቶች ላይ በመገኘትና ንግግር በማድረግ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን በተመለከተ የማስተዋወቅ ተግባራትን እንደሚያከናውን ይጠበቃል። በፍሬህይወት ረታ #EthiopianBroadcastingCorporation#Ethiopia#DigitalID#fayda#NationalID#DigitalEthiopia