@ebcnewsnow · Post #52333 · 12.03.2026 г., 15:00
በጋሞ ዞን በደረሰው የመሬት ናዳ አደጋ የሟቾች ቁጥር 70 ደረሰ ******************* በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ደጋማ አካባቢዎች በደረሰው ድንገተኛ የመሬት ናዳ የሟቾች ቁጥር 70 መድረሱን የክልሉ መንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል። የአገልግሎቱ ኃላፊ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በአራት ወረዳዎች በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የደረሰው ጉዳት አሁንም እየተጣራ መሆኑንና ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል። በአደጋው ሳቢያ ከ3,480 በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በአርባ ምንጭ ከተማ የኩልፎ ወንዝ ሙላትን ጨምሮ 190 ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። መንግሥት በአሁኑ ወቅት የሟቾችን አስክሬን የመፈለግና ተጎጂዎችን ከስጋት ቀጠና የማንሳት ሥራ እያከናወነ ይገኛል። ለተጎጂዎች በወረዳ፣ በዞንና በክልል ደረጃ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን የገለጹት ኃላፊው፤ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ዜጎች እንዲሁም በጎ አድራጎት ድርጅቶች በጋሞ ዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት የባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000321312865 ድጋፍ በማድረግ ከወገኖቻችሁ ጎን እንድትቆሙ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። በተመስገን ተስፋዬ #ጋሞ#ኢትዮጵያ#Gamo#Landslide#Ethiopia