@addisstandardamh · Post #7744 · 27/02/2026 08:33
#ኢንሳ ሰባተኛውን ጠቅላላ የምርጫ ሂደትን ተገን በማድረግ የ #ዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን ኢላማ ያደረገ ሰፊ የሳይበር ጥቃት እየተፈፀመ እንደሚገኝ አስታወቀ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ( #INSA) በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተለይም ሰባተኛውን ጠቅላላ የምርጫ ሂደትን ተገን በማድረግ፣ አጥፊዎች ስልታቸውን ይበልጥ በማወሳሰብ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን ኢላማ ያደረገ ሰፊ የሳይበር ጥቃት እየፈጸሙ እንደሚገኝ ከሚደርሱኝ መረጃዎችና የሳይበር ደህንነት ትንተናዎች ማረጋገጥ ችያለሁ አለ። አስተዳደሩ ባስተላለፈው አስቸኳይ የጥንቃቄ መልዕክቱ ላይ ጥቃቱ በተለይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ተማሪዎችን፣ በርቀት ሆነዉ በዲጂታል አማራጮች የሚማሩ ግለሰቦችን እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ኢላማ ያደረገ መሆኑን ነው የገለፀው። የመረጃ መንታፊዎች ከሚጠቀሙባቸዉ ዋና ዋና የጠለፋ ስልቶች መካከልም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊ በመምሰልና የፓርቲዎችን አርማ በመጠቀም "ለፓርቲያችን ድጋፍዎን እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ይግለጹ" ወይም "የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናችንን ይቀላቀሉ" የሚሉ አሳሳች መልዕክቶችን መላክ አንዱ መሆኑን ጠቁሟል። በተጨማሪም "የምርጫ ጣቢያዎትን ለማወቅ"፣ "የዕጩዎችን ዝርዝር ለማየት" ወይም "የምርጫ ውጤቶችን በቅድሚያ ለማግኘት" የሚሉ አሳሳች ማስፈንጠሪያዎችን (Links) በመጠቀም የተጠቃሚዎችን የዋትስአፕ አካውንት በቁጥጥራቸው ስር እንደሚያውሉ አመልክቷል። አስተዳደሩ በጥንቃቄ መልዕክቱ ተከታታይ ጠለፋ እና የማንነት ስርቆት ሌላኛው ስልት መሆኑን የገለፀ ሲሆን ይህ ስልት እጅግ አደገኛ የሆነው ጥቃቱ የሚመጣው ከሚታወቅና ከቅርብ ሰው በመሆኑ ነው ብሏል። ተጨማሪ ያንብቡ: https://www.facebook.com/share/1bKRq7WLAo/