Postinhoud
ኢራን አዲስ የሰላም ዕቅድ ለአሜሪካ አቀረበች ******************** ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ቀጣናዊ ውጥረቱን ለማርገብና የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማፅናት ያለመ አዲስና የተሻሻለ የሰላም ዕቅድ በፓኪስታን በኩል ለአሜሪካ ማቅረቧ ተገልጿል። ምንም እንኳን የሰላም ዕቅዱ ዝርዝር ይፋ ባይደረግም፣ እርምጃው በቀጣናው ያለውን ከፍተኛ ውጥረት ለማቃለል ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስከአሁን በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ምላሽ ባይሰጡም፣ የፖለቲካ ተንታኞች ግን የቴህራን አዲስ ዕቅድ አሜሪካ በኢራን ወደቦችና መርከቦች ላይ የጣለችው ማዕቀብ ከፈጠረው የኢኮኖሚ ጫና ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገምታሉ። በተለይም አሜሪካ በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ እያደረገችው ያለው ጥብቅ ቁጥጥር የኢራን የነዳጅ ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረጉ፣ ሀገሪቱን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመመለስ ዋነኛው ገፊ ምክንያት ሆኗል ተብሎ ተገምቷል። ይሁን እንጂ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የመተማመን ክፍተት አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን የኑክሌር እንቅስቃሴ ለሰላሙ ዋነኛ እንቅፋት ስለመሆኑ ሲናገሩ፣ በቴህራን በኩል ደግሞ የአሜሪካ የሆርሙዝ ሰርጥ ቁጥጥር ለስምምነቱ አለመሳካት ቀዳሚው ምክንያት ነው በማለት ትገልጻለች። ይህ የኢራን አዲስ የሰላም ዕቅድ በቀጣናው የጂኦፖለቲካ ሚዛን ላይ ለውጥ ያመጣ እንደሆነ በቅርቡ የሚታይ ይሆናል። በሀብተሚካኤል ክፍሉ #MiddleEast#Geopolitics#Iran#USA#Hormuz#PeaceTalks