@ebcnewsnow · Post #54311 · 2026/05/04 13:21
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በ3.3 ቢሊዮን ብር ወጪ በጣና ዳርቻ የሚገነባውን ግዙፍ የሆቴል ፕሮጀክት አስጀመሩ *************************** ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ፣ በጣና ሐይቅ ዳርቻ የሚገነባውን ግዙፍ እና ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻ ግንባታ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል። ይህ 4PBS (ፎር ፖይንት ባይ ሸራተን) በሚል ስያሜ የሚገነባው ሆቴል፤ ታሪካዊውን ጣና ሆቴል ዘመኑን በዋጀና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ዳግም ለመገንባት ያለመ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤ የሚገነባው ግዙፍ ፕሮጀክት የከተማዋን የቱሪዝም ገጽታ ወደ ላቀ ከፍታ የሚያሸጋግርና የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸዋል። ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተለያዩ የልማት ዘርፎች እያመጣ ያለውን ለውጥ ያደነቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንንም ፕሮጀክት በስኬትና በተቀመጠለት ጊዜ የማጠናቀቅ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል። ለፕሮጀክቱ ግንባታ 3.3 ቢሊዮን ብር በጀት የተያዘ ሲሆን፣ በግንባታው ሂደትም ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ግብዓቶች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተመላክቷል። በአሸናፊ እንዳለ #EthiopianBroadcastingCorporation#Ethiopia#TourismDevelopment#BahirDar#MidrocInvestmentGroup#LakeTana