@ebcnewsnow · Post #53721 · 19.04.2026 г., 09:58
"ከአሜሪካ ጋር ድርድሩ ቢቀጥልም ለስምምነት ገና ነን" - ኢራን ******************* ኢራን ከአሜሪካ ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች መግባባት ቢኖርም በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አሁንም ልዩነቶች እንዳሉ ገለፀች፡፡ የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባጋር ጋሊፍ፣ በኢራን እና አሜሪካ መካከል እየተካሄዱ ባሉ ውይይቶች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ወደ መግባባት መደረሱን አመልክተዋል። አፈ ጉባኤው ከአሜሪካ ጋር ንግግሮች መቀጠላቸውን ገልጸው፣ ነገር ግን አሁንም በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ልዩነቶች እንዳሉ ተናግረዋል። ኢራን በአሜሪካ የተጣሉባት ማዕቀቦች እንዲነሱላት ግፊት እያደረገች ሲሆን፣ አሜሪካ በበኩሏ በኢራን ያለው የኒውክሌር ፕሮግራም ሙሉ በሙሉ እንዲቆም መፈለጓ ሁለቱ ሀገራት ስምምነት ላይ ያለመድረሳቸው ዋነኛው ጉዳይ ነው ተብሏል። የፖለቲካ ተንታኞች፣ ይህ የሁሉቱ ሀገራት ሁኔታ ቀስ በቀስ እየተካሄደ ያለ የዲፕሎማሲ ሂደት መሆኑን ጠቅሰው፤ ውይይቶቹ ቢቀጥሉም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ፊርማ የሚመራ ስምምነት ላይ ለመድረስ ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል። ከዚህ በፊት ያለ ስምምነት የተጠናቀቀው የኢስላማባዱ የሰላም ስምምነት ለሁለተኛ ዙር ይደረጋል እየተባለ በሚገኝበት በዚህ ሰዓት፣ ኢራን እና አሜሪካ አንዳቸው በሌላኛው ላይ ጫና ለማድረግ እየሞከሩ እንደሆነ አልጀዚራ ዘግቧል። በሀብተሚካኤል ክፍሉ #EthiopianBroadcastingCorporation#Iran#USA#Diplomacy#GlobalSecurity