TGTGInsighttelegram intelligenceLIVE / telegram public index
← EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation)
EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation) avatar

TGINSIGHT POST

Post #51707

@ebcnewsnow

EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation)

Weergaven11,000Weergaven van post
Geplaatst17 feb17-02-2026, 05:24
Inhoud

Postinhoud

የአታቱርክ ፈር ቀዳጅነት እና የፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የኢትዮጵያ ጉብኝት፤ የሁለቱ ታላላቅ ሀገራት አዲስ ምዕራፍ *********************** በታሪክ ማኅደር ውስጥ አንዳንድ መሪዎች ሀገርን ያስተዳድራሉ፤ ጥቂቶች ደግሞ ሀገርን ዳግም ይፈጥራሉ። ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ በቱርካውያን ልብ ውስጥ የነገሠው ዝም ብሎ መሪ ስለነበረ አይደለም፤ ሊጠፋ የነበረን ማንነት ከሞት አፋፍ መልሶ በጠንካራ መሠረት ላይ የገነባ “የሀገር አዳኝ” ስለሆነ እንጂ። ዛሬም ድረስ በቱርክዬ መኖሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በገንዘብ ኖቶች ላይ ገዝፎ የሚታየው የእርሱ ምስል የናፍቆት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት ምልክት ነው። ለ600 ዓመታት ዓለምን ሲያናውጥ የነበረው የታላቁ ኦቶማን ኢምፓየር ግርማ ሞገስ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ አከተመለት። በአራት ማዕዘን የተከበበችው ቱርክዬ በወራሪዎች እጅ ልትቀራመት፣ ስሟም ከታሪክ ገጽ ሊፋቅ ጫፍ ደርሶ ነበር። የውስጥ መከፋፈልና የውጭ ወረራ ሀገሪቱን እንደ እሳት ሲለበልቧት፣ ቱርካዊ ነኝ ማለት ብርቅ ሊሆን ጥቂት ቀርቶት ነበር። በዚህ በጨለማ የተዋጠ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነበር ሙስጠፋ ከማል እንደ ብርሃን ብቅ ያለው። ማንም ይሳካለታል ብሎ ባልገመተበት ወቅት፣ ተስፋ የቆረጠውን ሕዝብ አስተባብሮና የወታደራዊ መኮንንነት ጥበቡን ተጠቅሞ በጋሊፖሊ ጦርነት ወራሪዎችን ድል በማድረግ የትንሣኤውን መንገድ መረቀ። አታቱርክ ንጉሣዊውን (የሱልጣኔት) ሥርዓት በማስወገድ በ1923 ዓ.ም የቱርክዬ ሪፐብሊክን ሲመሠርት፣ ዓላማው ሥልጣን መያዝ ብቻ አልነበረም፤ የዘመናት የኋላ ቀርነት ሰንሰለትን ሰብሮ ሀገሩን ወደ ሥልጣኔ ማማ ማውጣት እንጂ። እርሱ የፈጠራት ቱርክ በሃይማኖትና በዘር የተከፋፈለች ሳትሆን፣ በብሔራዊ አንድነትና በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ የቆመች ጠንካራ ሀገር ናት። ሃይማኖትን ከፖለቲካ በመለየት፣ ኢንዱስትሪን በማስፋፋትና የትምህርት ሥርዓቱን በማዘመን ቱርክን በዓለም አቀፍ መድረክ የምትከበር ሀገር አደረጋት። ዛሬ የምናያቸው ግዙፍ ግድቦች፣ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያዎችና የሥልጣኔ ተቋማት ሁሉ የእርሱ ራዕይ ፍሬዎች ናቸው። ሕዳር 1 ቀን 1938 ዓ.ም አታቱርክ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም፣ ዐሻራው ግን ሕያው ነው። በየዓመቱ በዚህ ዕለት በመላው ቱርክ ሕይወት ለሁለት ደቂቃ የቆመች እስክትመስል መኪኖች ይቆማሉ፣ ፋብሪካዎች ይዘጋሉ፣ ዜጎችም በዝምታ የሕሊና ጸሎት ያደርጋሉ። ይህ ዝምታ ለታላቁ መሪ የሚሰጥ የክብር ምስክርነት ነው። ቱርካውያን ዛሬም ችግር ሲገጥማቸው የሚሰባሰቡበት፣ ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚለኩበትና አንድነታቸውን የሚያጸኑበት መለኪያቸው አታቱርክ ነው። እርሱ ከቁልቁለት የታደጋት ሀገር ዛሬ የሥልጣኔ ጎዳናዋን በልበ ሙሉነት እየተጓዘች ትገኛለች። ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ሀገር ከውድቀት ተነስቶ እንዴት እንደሚገነባ ለዓለም ያሳየ የታሪክ ድንቅ ሥራ ነው። ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በአታቱርክ ብርቱ እጆች የታነጸችው ዘመናዊቷ ቱርክ፣ ዛሬ በዓለም አቀፉ መድረክ ገዝፋ የምትታይ የኃያልነት ተምሳሌት ሆናለች። ይህች ከውድቀት ተነሥታ የሥልጣኔ ማማ ላይ የወጣች ሀገር፣ በታሪክ አጋጣሚዎቿና በጠንካራ መሠረቷ ምክንያት በዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ ያላት ስፍራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናኘ መጥቷል። የዛሬዋ ቱርክ ትላንት አታቱርክ በዘራው የጥንካሬ ዘር እና ዛሬ በዓለም መድረክ በምታሳየው ተሰሚነት የብዙዎችን ቀልብ መሳቧን ቀጥላለች። ይህንን የታላቅነት ግርማ የተላበሰች ሀገር የሚመሩት የቱርኪዬ ፕሬዚደንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን፣ ዛሬ በታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ። የሁለቱ ታላላቅ ሀገራት መሪዎች መገናኘትም በምሥራቅ አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ ይታመናል። በዚህ ጉብኝት ወቅትም የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር ይበልጥ የሚያጠናክሩ፣ ለቀጣናው ዕድገት ፋይዳ ያላቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች እንደሚፈረሙ ይጠበቃል። #EBC#ebcdotstream#Ethiopia#turkiye