TGTGInsighttelegram intelligenceLIVE / telegram public index
Terug naar kanalen
EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation) avatar

TGINSIGHT CHAT

EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation)

@ebcnewsnow

News and media

EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation) @etvafaanoromoo1 @ETVkidschannel @EBCWORLD1 @etventertainment1

Abonnees13.5万Huidige kanaalabonnees
Gevolgde posts1,008Geïndexeerde posts
Recent bereik107,470Som van recente weergaven
Recente posts

Recente posts

Tag: #turkiye · 12 posts

当前筛选 #turkiye清除筛选

ኢትዮጵያና ቱርክዬ፦ በታሪክና በእምነት የተገመደው ወዳጅነት! ********************* ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ በይፋዊ የሥራ ጉብኝት ላይ የሚገኙት የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ዛሬ በአዲስ አበባ የሁለትዮሽ ውይይት ካደረጉ በኋላ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን በመግለጫቸው፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያው የእስልምና መዳረሻ እና የፍትሐዊው ንጉሥ ነጃሺ መገኛ መሆኗ ለሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር ትልቅ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ያላት የላቀ ሚና ለቱርክዬ ሁሌም ትልቅ ትርጉም እንዳለው ፕሬዚዳንቱ አንስተው፤ ይህ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ወዳጅነት ዛሬም በልማት እና በዲፕሎማሲያዊ ትብብር ደምቆ መቀጠሉን አክለዋል። የቱርክዬ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (TIKA) ታሪካዊውን የንጉሥ ነጃሺ መስጂድ እና የንጉሡን መካነ መቃብር ዕድሳት ማጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ይህም የሁለቱን ሀገራት እና ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል። የቱርክዬ ማሪፍ ፋውንዴሽንም በሀገራቸው እና በኢትዮጵያ መካከል የትምህርትና የባህል ድልድይ በመሆን የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ይበልጥ የማቀራረብ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን በመግለጫቸው አረጋግጠዋል። በላሉ ኢታላ #Ethiopia#Turkiye#Diplomacy#History#KingNajashi#RecepTayyipErdoğan#EthiopianBroadcastingCorporation#EBC#EBCdotstream

10,100 views

ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ በጋራ ለመፈፀም የተግባቡባቸው የስምምነት አጀንዳዎች እና ነጥቦች ************** ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር በብሔራዊ ቤተመንግሥት በሰጡት የጋራ መግለጫ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ለመፈፀም የተግባቡባቸውን የስምምነት አጀንዳዎች እና ነጥቦች ዘርዝረዋል። I. የንግድ እና ኢኮኖሚ ትብብር ✅ የንግድ ልውውጥ መጠን፦ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ቢያንስ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እና ከዚያም በላይ ለማሳደግ ታቅዷል። ✅ የዘርፍ ብዝሃነት (Diversification)፦ የንግድ ግንኙነቱ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ብቻ ሳይወሰን የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎችን እንዲያካትት ስምምነት ላይ ተደርሷል። ✅ የቱርክዬ ኢንቨስትመንት፦ ታዋቂ የቱርክዬ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ለሀገር ውስጥ እና ለጠቅላላው የአፍሪካ ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን እንዲያመርቱ እና ኤክስፖርት እንዲያደርጉ ድጋፍ ለማድረግ ተስማምተዋል። II. የባህር በር እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ✅ ኢትዮጵያ ያቀደችውን የ10.2 በመቶ ዕቅድ ለማሳካት የባህር በር ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል። ✅ ለኢትዮጵያ ዕድገት ማነቆ (bottleneck) የሆነውን የሎጂስቲክስ ችግር ለመፍታት የባህር በር ቁልፍ መሆኑ ታምኖበታል። ✅ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር እንድታገኝ ቱርክዬ በዲፕሎማሲው መስኩ የራሷን ጫና በመፍጠር የበኩሏን ሚና እንድትጫወት ከስምምነት ተደርሷል። III. የፀረ-ሽብር ትግል እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ✅ ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ በፀረ-ሽብር ትግሉ ዙሪያ በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል። ✅ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ቱርክዬ ዘንድሮ የምታዘጋጀውን የኮፕ (COP) ስብሰባ በሚቀጥለው ዓመት ለኢትዮጵያ የምታስረክብ በመሆኑ፣ በዝግጅት ሂደት ውስጥ የልምድ ልውውጥ እና መደጋገፍ ለማድረግ ተስማምተዋል። IV. ሥልታዊ እና ቀጣናዊ ግንኙነት ✅ አፍሪካ በቀጣይ 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ የሚኖራትን ከፍተኛ የኢኮኖሚ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቱርክዬ በአፍሪካ ዕድገት ውስጥ ያላትን የጂኦግራፊያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሚና እንድትወጣ መግባባት ላይ ተደርሷል። ✅ በኢትዮጵያ እና በቱርክዬ መካከል ያለውን ጥንታዊ ግንኙነት በመከባበር እና በመደጋገፍ ላይ ተመሥርቶ ይበልጥ ለማጠናከር መሪዎቹ ቃል ገብተዋል። #Ethiopia#Turkiye#Diplomacy#AbiyAhmedAli#RecepTayyipErdoğan#EthiopianBroadcastingCorporation#EBC#EBCdotstream

8,350 views

"ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላት አስፈላጊነት ይበልጥ እያደገ መጥቷል" - ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ********* የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ላስመዘገቡት ስኬት “እንኳን ደስ አለዎት” በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ይህን ያሉት ዛሬ በብሔራዊ ቤተመንግሥት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ፥ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ በርካታ ስምምነቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ስምምነቶቹ ባቡርን ጨምሮ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ የፋብሪካዎች ግንባታ፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ እና የቱሪዝም ልማትን እንደሚያካትቱ አብራርተዋል። ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ረጅም የሀገረ መንግሥት ታሪክ እና የተረጋጋ አስተዳደር ያላት ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት አስፈላጊነቷ ይበልጥ እያደገ መጥቷል ብለዋል። ቱርክዬ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠረ ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ ከፍተኛ ትኩረት እንደምትሰጥም አክለዋል። በላሉ ኢታላ #Ethiopia#Turkiye#Diplomacy#AbiyAhmedAli#RecepTayyipErdoğan#EthiopianBroadcastingCorporation#EBC#EBCdotstream

10,100 views

“130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር የባሕር በር አጥታ ተዘግቶባት መኖር እንደሌለባት ከቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር ተወያይተናል” - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ************************** "130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር የባሕር በር አጥታ ተዘግቶባት መኖር እንደሌለባት እና ሀገራችን የባህር በር በሰላማዊ መንገድ ማግኘት የምትችልበት ሁኔታ ላይ እንዲያግዙ ከቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር ተወያይተናል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በብሔራዊ ቤተመንግሥት የጋራ መግለጫ እየሰጡ ይገኛሉ። #EBC#ebcdotstream#Ethiopia#PMAbiy#RecepTayyipErdoğan#Turkiye#Diplomacy

8,800 views

የኢትዮ-ቱርክዬ ስትራቴጂካዊ አጋርነት አዲስ ምዕራፍ ************ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር በሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል። ይህ በሁለቱ ሀገራት በመሪዎች ደረጃ የተደረገው ምክክር በኢትዮጵያ እና በቱርክዬ መካከል ለዘመናት የዘለቀውንና በታሪክ የተፈተነውን ወዳጅነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ነው። የመሪዎቹ ውይይት በስትራቴጂካዊ የትብብር መስኮች ላይ ትኩረት ያደረገ ጥልቅ የሐሳብ ልውውጥ ተካሂዶበታል። ሁለቱ መሪዎች የሀገራቱን የጋራ ጥቅም የሚያስከብሩ አጋርነቶችን ይበልጥ ለማሳደግ ያላቸውን ፅኑ ቁርጠኝነት ዳግም አረጋግጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው፥ ይህ ዘላቂ ግንኙነትና በስትራቴጂካዊ መስኮች የተጀመረው ጠንካራ ትብብር የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች የሚያስተሳስረውን ወዳጅነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ይህ ታሪካዊ ግንኙነት ለሁለቱም ሀገራት ብልፅግና ብቻ ሳይሆን ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትም ያለው ፋይዳ የላቀ እንደሚሆን ይጠበቃል። #Ethiopia#Turkiye#PMAbiyAhmed#PresidentErdogan#Diplomacy#StrategicPartnership#AddisAbaba#Ankara

7,870 views

‎"ከአንካራ እስከ አዲስ አበባ፤ በሁለቱ ጥንታዊ ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክሩ እና ዘላቂ ትስስርን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ውይይቶች እንዲኖሩን እመኛለሁ" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) #EthiopianBroadcastingCorporation#Ebcdotstream#Ethiopia#PMAbiy#RecepTayyipErdoğan#Turkiye#Diplomacy

8,430 views

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን ደማቅ አቀባበል አደረጉ ******************* ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቱርክዬ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ረጅብ ጣይፕ ኤርዶዋን በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ይፋዊ ጉብኝት ዛሬ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው ተቀብለዋቸዋል። ይህ ጉብኝት በቱርክዬ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን እያደገ የመጣ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚያጎላ ሲሆን፤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ሚናም የሚያረጋግጥ ነው። #EthiopianBroadcastingCorporation#Ebcdotstream#Ethiopia#PMAbiy#RecepTayyipErdoğan#Turkiye#Diplomacy

8,440 views

እንኳን ደህና መጡ! የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ #EthiopianBroadcastingCorporation#Ebcdotstream#Ethiopia#PMAbiy#RecepTayyipErdoğan#Turkiye#Diplomacy

7,860 views

የቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን አዲስ አበባ ገቡ ************** ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለቱርክዬ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ወደ ምድረ ቀደምቷ ሀገር ኢትዮጵያ እንኳን በደህና መጡ በማለት ሞቅ ያለ አቀባበል ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ይህ ታሪካዊ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈ፣ በሁለቱ ጥንታዊ ሀገራት መካከል ያለውን "ጥልቅ የአጋርነት ጥንካሬ" የሚያንጸባርቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና መልዕክት፦ "ይፋዊ የስራ የጉብኝት ልውውጣችን በቱርክዬ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ጥልቅ የአጋርነት ጥንካሬ የሚያንጸባርቅ ነው። በአንካራ እና በአዲስ አበባ መካከል ያለውን ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክሩ እና ዘላቂ ትስስርን የሚያረጋግጡ ውጤታማ ውይይቶች እንዲኖሩን እመኛለሁ።" ይህ ጉብኝት በምሥራቅ አፍሪካና በዩራሺያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የስትራቴጂካዊ ትስስር ወደ አዲስ ከፍታ ያሸጋግራል ተብሎ ይጠበቃል። #EthiopianBroadcastingCorporation#Ebcdotstream#Ethiopia#PMAbiy#RecepTayyipErdoğan#Turkiye#Diplomacy

8,140 views

ለቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በ2007 የተሰጠው ታሪካዊ ዕውቅና ******************** የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለቱርክዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል ምክንያት፦ ለአፍሪካ ሰላም፣ ለዲሞክራሲና ለኢኮኖሚ ዕድገት ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ። ዕውቅናው የተሰጠበት ቀን፦ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም #EthiopianBroadcastingCorporation#Ebcdotstream#Ethiopia#Turkiye#Diplomacy

9,440 views

ኢትዮጵያ እና ቱርክዬ - ለግማሽ ሚሌኒየም የዘለቀ ወዳጅነት *********************** ታውቃላችሁ? የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ግንኙነት የትናንት ሳይሆን የግማሽ ሚሌኒየም ታሪክ ውጤት ነው። ከቀይ ባሕር ዳርቻ እስከ ዓባይ ተፋሰስ የዘለቀው ይህ ዕድሜ ጠገብ ወዳጅነት፣ በታሪክ አጋጣሚዎች ሳይገታ ዛሬም በጽኑ መሠረት ላይ ይገኛል። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በ16ኛው ክፍለ ዘመን በኦቶማን ኢምፓየር ዘመን የጀመረ ረጅም ታሪክ ያለው ሲሆን፣ በ1912 ዓ.ም በሐረር ከተማ የመጀመሪያው የቆንስላ ጽሕፈት ቤት መከፈቱ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ ትልቅ ምዕራፍ ሆኗል። ይህ ግንኙነት በንግድ እና በዲፕሎማሲ ብቻ ሳይወሰን በባህል እና በሃይማኖት ትሥሥር ጭምር የጎለበተ ነው። ዛሬ ላይ ቱርክዬ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ቀዳሚ የውጭ ኢንቨስተሮች አንዷ ስትሆን፣ በተለይም በጨርቃጨርቅ፣ በግንባታ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚታየው ትብብር ለሺዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በተጨማሪም የቱርክዬ አየር መንገድ (Turkish Airlines) እና የልማት ድርጅቱ (TIKA) የሁለቱን ሀገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ይበልጥ በማቀራረብ ረገድ እንደ ድልድይ እያገለገሉ ይገኛሉ። "ወዳጅነት እንደ ወይን ጠጅ ነው፤ በቆየ ቁጥር ይጣፍጣል" እንደሚባለው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ እና የቱርክዬ ግንኙነትም በዘመናት ፈተና ውስጥ አልፎ ዛሬ ላይ ለቀጣናዊ ሰላም እና ብልጽግና ዋስትና ሆኗል። ይህ ለ500 ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት፣ ለቀጣዩ ትውልድ በጋራ የማደግ እና የመበልጸግ ትልቅ አርአያ ሆኖ ይቀጥላል። #Ethiopia#Turkiye#History#Friendship#Diplomacy#Africa#Europe

8,940 views

የአታቱርክ ፈር ቀዳጅነት እና የፕሬዝዳንት ኤርዶዋን የኢትዮጵያ ጉብኝት፤ የሁለቱ ታላላቅ ሀገራት አዲስ ምዕራፍ *********************** በታሪክ ማኅደር ውስጥ አንዳንድ መሪዎች ሀገርን ያስተዳድራሉ፤ ጥቂቶች ደግሞ ሀገርን ዳግም ይፈጥራሉ። ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ በቱርካውያን ልብ ውስጥ የነገሠው ዝም ብሎ መሪ ስለነበረ አይደለም፤ ሊጠፋ የነበረን ማንነት ከሞት አፋፍ መልሶ በጠንካራ መሠረት ላይ የገነባ “የሀገር አዳኝ” ስለሆነ እንጂ። ዛሬም ድረስ በቱርክዬ መኖሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በገንዘብ ኖቶች ላይ ገዝፎ የሚታየው የእርሱ ምስል የናፍቆት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነት ምልክት ነው። ለ600 ዓመታት ዓለምን ሲያናውጥ የነበረው የታላቁ ኦቶማን ኢምፓየር ግርማ ሞገስ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ አከተመለት። በአራት ማዕዘን የተከበበችው ቱርክዬ በወራሪዎች እጅ ልትቀራመት፣ ስሟም ከታሪክ ገጽ ሊፋቅ ጫፍ ደርሶ ነበር። የውስጥ መከፋፈልና የውጭ ወረራ ሀገሪቱን እንደ እሳት ሲለበልቧት፣ ቱርካዊ ነኝ ማለት ብርቅ ሊሆን ጥቂት ቀርቶት ነበር። በዚህ በጨለማ የተዋጠ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነበር ሙስጠፋ ከማል እንደ ብርሃን ብቅ ያለው። ማንም ይሳካለታል ብሎ ባልገመተበት ወቅት፣ ተስፋ የቆረጠውን ሕዝብ አስተባብሮና የወታደራዊ መኮንንነት ጥበቡን ተጠቅሞ በጋሊፖሊ ጦርነት ወራሪዎችን ድል በማድረግ የትንሣኤውን መንገድ መረቀ። አታቱርክ ንጉሣዊውን (የሱልጣኔት) ሥርዓት በማስወገድ በ1923 ዓ.ም የቱርክዬ ሪፐብሊክን ሲመሠርት፣ ዓላማው ሥልጣን መያዝ ብቻ አልነበረም፤ የዘመናት የኋላ ቀርነት ሰንሰለትን ሰብሮ ሀገሩን ወደ ሥልጣኔ ማማ ማውጣት እንጂ። እርሱ የፈጠራት ቱርክ በሃይማኖትና በዘር የተከፋፈለች ሳትሆን፣ በብሔራዊ አንድነትና በዴሞክራሲያዊ እሴቶች ላይ የቆመች ጠንካራ ሀገር ናት። ሃይማኖትን ከፖለቲካ በመለየት፣ ኢንዱስትሪን በማስፋፋትና የትምህርት ሥርዓቱን በማዘመን ቱርክን በዓለም አቀፍ መድረክ የምትከበር ሀገር አደረጋት። ዛሬ የምናያቸው ግዙፍ ግድቦች፣ ዓለም አቀፍ የአየር ማረፊያዎችና የሥልጣኔ ተቋማት ሁሉ የእርሱ ራዕይ ፍሬዎች ናቸው። ሕዳር 1 ቀን 1938 ዓ.ም አታቱርክ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይም፣ ዐሻራው ግን ሕያው ነው። በየዓመቱ በዚህ ዕለት በመላው ቱርክ ሕይወት ለሁለት ደቂቃ የቆመች እስክትመስል መኪኖች ይቆማሉ፣ ፋብሪካዎች ይዘጋሉ፣ ዜጎችም በዝምታ የሕሊና ጸሎት ያደርጋሉ። ይህ ዝምታ ለታላቁ መሪ የሚሰጥ የክብር ምስክርነት ነው። ቱርካውያን ዛሬም ችግር ሲገጥማቸው የሚሰባሰቡበት፣ ብሔራዊ ጥቅማቸውን የሚለኩበትና አንድነታቸውን የሚያጸኑበት መለኪያቸው አታቱርክ ነው። እርሱ ከቁልቁለት የታደጋት ሀገር ዛሬ የሥልጣኔ ጎዳናዋን በልበ ሙሉነት እየተጓዘች ትገኛለች። ሙስጠፋ ከማል አታቱርክ ሀገር ከውድቀት ተነስቶ እንዴት እንደሚገነባ ለዓለም ያሳየ የታሪክ ድንቅ ሥራ ነው። ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት በአታቱርክ ብርቱ እጆች የታነጸችው ዘመናዊቷ ቱርክ፣ ዛሬ በዓለም አቀፉ መድረክ ገዝፋ የምትታይ የኃያልነት ተምሳሌት ሆናለች። ይህች ከውድቀት ተነሥታ የሥልጣኔ ማማ ላይ የወጣች ሀገር፣ በታሪክ አጋጣሚዎቿና በጠንካራ መሠረቷ ምክንያት በዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ ያላት ስፍራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናኘ መጥቷል። የዛሬዋ ቱርክ ትላንት አታቱርክ በዘራው የጥንካሬ ዘር እና ዛሬ በዓለም መድረክ በምታሳየው ተሰሚነት የብዙዎችን ቀልብ መሳቧን ቀጥላለች። ይህንን የታላቅነት ግርማ የተላበሰች ሀገር የሚመሩት የቱርኪዬ ፕሬዚደንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን፣ ዛሬ በታሪካዊቷ ኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ። የሁለቱ ታላላቅ ሀገራት መሪዎች መገናኘትም በምሥራቅ አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ ይታመናል። በዚህ ጉብኝት ወቅትም የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ትሥሥር ይበልጥ የሚያጠናክሩ፣ ለቀጣናው ዕድገት ፋይዳ ያላቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች እንደሚፈረሙ ይጠበቃል። #EBC#ebcdotstream#Ethiopia#turkiye

11,000 views